ሪፖርት | አዳማ ከተማ ኤሌክትሪክን ረቷል

የትግራይ ክልል ክለቦችን ለመተካት ሁለተኛ አማራጭ የሆነው የስድስቱ ክለቦች የዙር ውድድር ዛሬ የተጀመረ ሲሆን በሁለተኛ የጨዋታ መርሀግብር አዳማ ከተማ በኤልያስ አህመድ ብቸኛ ጎል ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1ለ0 አሸንፏል፡፡

በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እጅግ ሳቢ በነበረው ነገር ግን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ደካማ በሆነው የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ላይ ቡድኖቹ እምብዛም ከግብ ጠባቂ ጋር ለመገናኘት ጥረት ሲያደርጉ አልታየም። 20 ደቂቃዎችን አንድም የጠራ የግብ ሙከራ ባላየንበት ጨዋታም አዳማ ከተማ ረጃጅም ኳሶችን ወደ አጥቂዎቹ ማማዱ ኩሊባሊ እና ጀሚል ያዕቆብ በመጣል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ቢሞክርም የኤሌክትሪክን የግብ ክልል ለመሻገር ግን እጅጉን ከብዶት ታይቷል፡፡ቡድኑ በዚህኛው አጋማሽ በቀላሉ ሳጥን ውስጥ መገኘት ቢችሉም የኤሌክትሪክ ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት ማስከፈት ሳይችል ጨዋታው ቀጥሏል።


በግራ እና ቀኝ የመስመር አጨዋወት ላይ አድልተው የኤርሚያስ ኃይሉን እና የተሻ ግዛውን ፈጣን የጨዋታ አካሄድ ለመጠቀም የሞከሩት ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ሁለቱ ተጫዋቾች ከሳሙኤል ታዬ እግር በሚነሱ ኳሶች በደንብ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ሲሞክሩ ነበር። ቡድኑም ከአዳማ ከተማ በተሻለ ወደ ግብ ሲያመራ መረጋጋት ይታይበት ነበር። ይህ ቢሆንም ኤሌክትሪክ የመጀመሪያ ሙከራውን ያደረገው በ21ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በዚህም ሳሙኤል ታዬ ከመሐል ሜዳው ለየተሻ ግዛው ሰጥቶት ፈጣኑ አጥቂ ብቻውን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ የነበረ ቢሆንም ኳሰን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ በተመሳሳይ በ40ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ከመስመር ሲያሻማ ሳጥን ውስጥ የአዳማ ከተማ ተከላካዮች ለጥቂት በራሳቸው ላይ ሊያስቆጥሩ ቢቃረቡም ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል። የመጀመሪያው አጋማሽም ግብ ሳይስተናገድበት ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተሽለው መታየት ቢችሉም ይታይባቸው የነበረው ደካማ የአጨራረስ ብቃት የኃላ ኃላ ዋጋ ያስከፈላቸው ይመስላል፡፡ ጥቅጥቅ ባለ መከላከል በመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳስ ላይ ትኩረት አድርገው ወደ ሜዳ የገቡት የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ተጫዋቾች የኤሌክትሪክን ደካማ የአደራደር ስህተት በተደጋጋሚ ለመጠቀም ጥረቶች አልተለያቸውም።63ኛው ደቂቃ ላይም ሚሊዮን ሰለሞን በረጅሙ ወደ ጎል ሲያሻማ በኤሌክትሪክ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ዝንጉነት ነፃ ሆኖ የነበረው ኤልያስ አህመድ በቀላሉ ከመረብ አሳርፎ የዚህን ውድድር የመጀመርያ ጎል አስቆጥሯል፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ኤሌክትሪክ አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ቢችሉም የተለየ ነገር ሳይታይ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡