በዛሬው ሦስተኛ ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ሀምበርቾ ዱራሜን 1-0 አሸንፏል።
ሁለቱን የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ያገናኘው የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ መሪነት አምስት ያህል ደቂቃዎችን ዘግየት ብሎ ጀምሯል፡፡ቀዝቃዛማ አየር አጅቦት የጀመረው የመጀመሪያው አጋማሽ የኮልፌ ቀራኒዮ የበላይነት እጅግ ገዝፎ ሜዳ ላይ መታየት የቻለበት ነበር። በተለይ በአንድ ሁለት ቅብብል በአግባቡ ኳስን እያንሸራሸሩ በመጠቀሙ የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡ ከተረጋጋው የመሀል ሜዳ ክፍላቸው በቀኝ በኩል ወደ ተሰለፈው አንዋር ዱላ አድልተው መጫወታቸው ብልጫ ለመውሰዳቸው ማሳያ ነው፡፡ በተወሰነ መልኩ ከሚቋረጡ የኮልፌ የቅብብል ኳሶች አልያም በረጃጅሙ ወደ አጥቂው ዳግም በቀለ ኳስን በማሻገር ጎል ለማስቆጠር ሀምበሪቾዎች በተደጋጋሚ ይሄዱበት የነበረው ሂደት እምብዛም ፍሬያማ አልነበረም። በ10ኛው ደቂቃ ብሩክ ኤልያስ ለግራ መስመር ተከላካዩ አቤንኤዘር ኦቴ ሰጥቶት ተጫዋቹ ወደ ሳጥን ገፍቶ ከገባ በኋላ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ የጨወታው ጥሩ ሙከራ ነበረች፡፡
በተረጋጋ የቅብብል መንገድ በመጫወት የተዋጣላቸው የአሰልጣኝ መሀመድ ኑርንማው ኮልፌዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ እንደነበራቸው ብልጫ ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል፡፡ በመሀል ሜዳ ላይ በቅብብል የመጣውን ኳስ አንዋር ዱላ በቀኝ መስመር ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ሰጥቶት ደሳለኝ ወርቁ በሚገርም መረጋጋት ከመረብ አሳርፏታል፡፡ ብልጫ ሊወደስባቸው ግድ የሆነባቸው ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ወደ አጥቂው ዳግም በቀለ ኳሶችን ተደራሽ በማድረግ ለመንቀሳቀስ ቢጥሩም ውጤታማ ሊሆን አልቻሉም። በ42ኛው ደቂቃ ዳግም አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው አብኪዳን ኪዳነማርያም ይዞበታል፡፡ አጋማሹም በኮልፌ 1-0 መሪነት ተገባዷል፡፡
ተመጣጣኝነት በተወሰነ መልኩ በተንፀባረቀበት ሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ባለ ዝናብ ታጅቦ እስከ ፍፃሜው የዘለቀበት ነበር፡፡ ከመጀመሪያው አጋማሽ በመጠኑም ቢሆንም መቀዛቀዝ የታየባቸው ኮልፌ ቀራኒዮዎች ኳስን በመቆጣጠር ረገድ ወጥነት አይኑራቸው እንጂ እጅግ መልካም የሚባለውን ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ከመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ መሻሻሎች የታየባቸው ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በዳግም በቀለ ላይ ጥገኛ ይመስል የነበረን እንቅስቃሴን ቢኒያም ጌታቸው ተቀይሮ እስኪገባ ድረስ ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ በ59ኛው ደቂቃ አማካዩ ዋቁማ ዲንሳ ወደ ግብ ክልል ሲያሻማ ዳግም በቀለ በግንባር ገጭቶ ንቁ ሆኖ በጨዋታው የታየው ግብ ጠባቂው አብኪዳን ኪዳነማርያም የያዘበት ሙከራ ነው፡፡
በዚህኛው አጋማሽ ይበልጡኑ ጥንቃቄ ላይ ትኩረት ያደረጉት ኮልፌዎች 64ኛው ደቂቃ የመስመር ተከላካዩ ዳዊት ቹቹን በሁለት ቢጫ ካርድ በቀይ ካርድ አጥተዋል፡፡ ኮልፌዎች ያገኙትን የእጅ ውርወራ ተጫዋቹ ለመወርወር በመዝግየቱ ቢጫ ካርድ ባገኘበት ቅፅበት ከኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ ጋር አላስፈላጊ ሰጣ ገባ ውስጥ በመግባቱ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል፡፡ በሌላ በኩል ሀምበሪቾ ዱራሜዎች አሁንም በዳግም በቀለ እና ተቀይሮ በገባው ቢኒያም ጌታቸው አማካኝነት ግብ ለማግኘት ታትረዋል፡፡
68ኛው ደቂቃ ነጋሽ ታደሰ በጥሩ ሁኔታ አቀብሎት ዳግም በቀለ ነፃ ቦታ ሆኖ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ በቀጥታ ቢመታውም ለጥቂት ኢላማዋን ስቷል፡፡ 73ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ብሩክ ሙሉጌታ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ይዞ የሄዳትን ኳስ ለግብ አስቆጣሪው ደሳለኝ ወርቁ በፍጥነት አቀብሎት ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የሳታት ኳስ የኮልፌዎችን የግብ መጠን የምታሳድግ አጋጣሚ ነበረች፡፡ የመጨረሻዎቹን 10 ደቂቃዎች በተለይ በቢኒያም ጌታቸው አማካኝነት በተደጋጋሚ ሀምበሪቾዎች ጎል ለማስቆጠር ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ጨዋታው በኮልፌ 1-0 ድል አድራጊነት ተጠናቋል፡፡