ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሠልጣኙን ውል አድሷል

ከአምስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን ውል አራዝሟል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ትልቅ ስም ያለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የሊጉን ዋንጫ ለአራተኛ ጊዜ ከፍ ማድረጉ ይታወቃል። ጥሩ ዓመት ያሳለፈው ቡድኑም በቀጣይ ዓመት ጠንካራነቱን ለማስቀጠል እና ከፊቱ ያለበትን የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር በጥሩ ሁኔታ ለመቅረብ ያለፉትን ቀናት ሥራዎችን ሲሰራ አሳልፏል። ክለቡ ፊቱን ወደ ተጫዋቾች ዝውውር ከማዞሩ በፊትም ውላቸው ሰኔ 30 የሚያልቀውን አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

22 ዓመታትን በአሠልጣኝነት ያሳለፉት አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከ2004 ጀምሮ እያሰለጠኑ እንደሚገኝ ይታወሳል። ከ2004 ጀምሮም ቡድኑ 4 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን ጨምሮ አጠቃላይ አስራ አንድ ዋንጫዎችን አስገኝተውለታል። በቀጣይ ሁለት ዓመታትም አሠልጣኙ ከክለቡ ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት መፈፀማቸው ታውቋል።