በኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ጅማ አባ ጅፋር መካከል ከተደረገው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞቹ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡
አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ስለ ጨዋታው
“በጨዋታው የመከላከል አደረጃጀታቸው ጠንካራ ነበር ፤ አይከፍቱም። ቀጥተኛ ኳስ ነው የሚጫወቱት እና ያንን ለመስበር ሁለት ሦስት ቀን ተነጋግረን ነው የገባነው። ጨዋታቸውን በዲኤስቲቭም አይ ነበር። አይሸነፉም ፤ ሁለተኛው ዙር ላይ በብዛት አቻ ይወጣሉ ማግባት ይከብዳል። ተከላካዩ ጠንካራ ነው። ያንን ለመስበር የአሰላለፍ ለውጥ አድርግ ነበር። ከባለፈው እነ አደምን ከፊት አድርጊያለሁ። አስገብቼው ነው ያገባነው ጎሉን እና በጣም ደስ ይላል፡፡ኳሱን ተቆጣጥረናል ባሰብነውም ልክ ሄዶልናል፡፡
የጅማን ረጃጅም ኳስ ለመቆጣጠር ስለከበዳቸው ሁኔታ
“ከዚህ በፊትም ሱፐር ሊግ የገባብን ጎል በኳስ እንቅስቃሴ ብልጫ አልነበረም። ተቀባብሎ የሚያገባብንም የለም ብዙ ጊዜ የቆመ ኳስ ነው የሚቆጠርብን። መከላከያ ያገባብን እና ባለፈውም አዳማ ያገባብን ጎል ተመሳሳይ ኳሶች ናቸው ናቸው፤ የቅጣት ምት ኳሶች ናቸው፡፡ ረጃጅም የሚጣሉትን ሸራርፈው ያገቡብናል። እና እዛም ላይ ለመስራት ሞክረናል። እኛ ኳሱ ላይ ብቻ ነው ያተኮርነው ግን ቡድናችን ይሄ ክፍተት አለበት። ለመስራት ሞክረናል አንድ ቀን እየቀረን። ልምምዳችን ላይ ለምንድነው እንዲህ ዓይነት ኳስ የሚገባብን ብለን ተነጋግረን ነበር ዛሬም የተፈተነው በዛ ነው፡፡
አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባ ጅፋር
ስለጨዋታው
“በውጤት ደረጃ ነጥብ ጥለናል በሜዳ ላይ በነበረው እንቅስቃሴ ኤልፓም ጠንክሮ ነው የመጣው። በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጥሩ ነበርን ግን ውጤቱን ወስደውብናል። እኛ ጋር ትንሽ ድክመቶች ይታያሉ። እንግዲህ ውድድሩ አላለቀም ከዚህም በኋላ ሦስት ጨዋታዎች ይቀሩናል። ለሁሉም ክለቦች ዕኩል ግምት ሰጥተን አሸናፊ ለመሆን እና በሊጉ ላይ ለመቆየት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡
በተደጋጋሚ ተጋጣሚ ግብ ክልል ደርሶ ስላለመጠቀም
“አሁን ውድድር ላይ ሆነን ይሄን ማስተካከል አንችልም። ባሉን ልጆች እየተጠቀምን ነው ያለነው። አሁንም ቢሆን ባለችን ጊዜ አስተካክለን ለመምጣት ነው እንጂ አጨራረሳችን ደካማ ነው። እነዚህን በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ አርመን ለመምጣት እንሞክራለን፡፡