ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጫዋቾቹን ውል ማደስ ጀምሯል

ከፊቱ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የዞን ማጣሪያ ውድድር የሚጠብቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአራት ተጫዋቾቹን ውል ማደሱ ታውቋል።

የዘንድሮ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2014 የሊጉ የውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የዞን የማጣሪያ ውድድሩ ያከናውናል። ከሐምሌ 10 እስከ 25 ድረስ (ጁላይ 17 – ኦገስት 1) በኬንያ አስተናጋጅነት በሚደረገው የቀጠናው ውድድር ላይ የሚሳተፈው የሀገራችን ተወካይ ንግድ ባንክም እስካሁን ዝግጅቱን ባይጀምርም በዚህ ሳምንት የአሠልጣኙን ብርሃኑ ግዛው እና ተጫዋቾችን ውል ለማደስ ሲንቀሳቀስ ሰንብቷል። በትናንቱ ዘገባችን እንደገለፅነውም ክለቡ የአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ያደሰ ሲሆን አሁን ደግሞ ፊቱን ወደ ተጫዋቾች በማዞር ውላቸው ያለቀባቸውን ተጫዋቾች ቆይታ ማራዘሙ ተገልጿል።

ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘው መረጃ መሠረት ስድስት ተጫዋቾችን ለመቀነስ የወሰነው ክለቡ የህይወት ደንጊሶን፣ ዓለምነሽ ገረመው፣ ፎዚያ መሐመድ እና ንግስቲ መዓዛን ውል አራዝሟል። ከዓለምነሽ ገረመው ውጪ ያሉት ሦስቱ ተጫዋቾች ለሁለት ዓመት ሲፈርሙ ዓለምነሽ ግን ለአንድ ዓመት ውሏ እንዲታደስ ተደርጓል።

የኬንያው ውድድር ሊጀመር 20 ቀናት ብቻ ቢቀሩትም ክለቡ እስካሁን ዝግጅት አለመጀመሩ አግራሞትን ፈጥሯል። በተለይ ተጫዋቾቹ ከመጋቢት 19 (የዘንድሮ የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ) በኋላ ምንም ጨዋታ አለማድረጋቸው እና ከውድድር መራቃቸው ሲታሰብ ክለቡ በቀጠናው ውድድር ላይ አሉታዊ ውጤት እንዳይመጣ አስግቷል። አሁን ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሠረት ደግሞ መዘግየቶች ቢኖሩም በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ (ረቡዕ) ተጫዋቾች ተሰባስበው ከአዲስ አበባ ውጪ ልምምዳቸውን እንደሚጀምሩ ተመላክቷል።

በተያያዘ ዜና የክረምት የዝውውር መስኮት በሚከፈትበት ጊዜ (ሐምሌ 1) አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለባቸው እንደሚቀላቅሉ ሰምተናል።