አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የት ይገኛሉ?

ላለፈው አንድ ዓመት ከክለብ እግር ኳስ የራቁት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የት ይገኛሉ?

በኢትዮጵያ እግርኳስ በሁለተኛው የሊግ እርከን በሆነው ከፍተኛ ሊግ ለበርካታ ዓመታት አሠልጥነዋል። በአስራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ መጨረሻ ላይ ባልጠበቁት መንገድ የአሰልጣኝነት መንበሩን ካገኙ በኃላ ተጫዋች እና አሰልጣኝ ሆነው የስልጠና ዓለሙን ዲላ ከተማን በማሰልጠን ሀ ብለው ጀምረዋል።

ዲላ ከተማን ለበርካታ ዓመታት ከማሰልጠን አልፈው በደቡብ ክልል የተለያዩ ዕድሜ ውስጥ ለሚገኙ እና ክልሉን ወክለው ለተወዳደሩ ስብስቦች አሠልጣኝ ሆነው አገልግለዋል ፤ በ2011 ከጥር ወር ጀምሮ ደግሞ ደቡብ ፓሊስን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አድገዋል። ለወራት ወላይታ ድቻን ካሰለጠኑ በኃላ ከክለቡ ጋር ተለያይተው ላለፈው አንድ ዓመት ከክለብ እግር ኳስ የራቁት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዬጵያ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ከእግር ኳስ የራቁበት ምክንያት…?

ከእግር ኳስ ብዙም አልራቅኩም። ከአንዳንድ ክለቦች ንግግር እያደረግኩ ነበር ፤ ግን በንግግሩ መሀል ክለቦቹ ሀሳባቸውን ቀይረው ሌላ ሰው ይቀጥራሉ። ከዛ ውጭም ግን በራሴ ምክንያት ያልተቀበልኳቸው ጥያቄዎች ነበሩ። አንዳንድ ምክንያቶች ከኮቪድ ወረርሺኝ ጋር የተያያዙ ናቸው። ሌላም ከከፍተኛ ሊግ ላይ አንዳንድ የቀረቡ ጥያቄዎች ነበሩ። በአካል ሄጄም አይቻቸው ነበር። ሆኖም መዋቅራቸው ብዙም አልተመቸኝም። መዋቅራቸው ጥሩ ያልሆኑ ክለቦች ገብተህ መስራት ከባድ ነው። ገንዘብ ሳይሆን ጥሩ የስራ ከባቢ ካለው ቡድን ጋር ነው መስራት የምፈልገው።

ጊዜዎን በምን እያሳለፉ ነው?

ዘንድሮ ቢያንስ ሦስት መፅሐፍ የሚወጣቸው ስድስት መቶ ገፅ የሚደርስ ፅሥሑፍ ፅፍያለው ፤ ሥራ አልፈታሁም።
ቡድን ቢኖረኝ አስር ዓመት የማሰለጥንበትን ነገር አዘጋጅቻለው። አብዛኛው ጊዜዬን በማንበብ እና በመፃፍ ነው የማሳልፈው።

ቀጣይ እቅድ…?

በሁሉም ረገድ ዝግጁ ነኝ። ክለቦች ፈልገውኝ እኔጋ ካልመጡ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ሰዎኝ ስር ተሸጉጬ ምለምነው ነገር የለኝም። ለፕሪምየር ሊጉም ለከፍተኛ ሊጉም የሚሆን በቂ ዝግጅት አድርጌ ለአዲስ ስራ እየተጠባበቅኩ ነው። ስራ ከተገኘ ለነገ የምለው ነገር የለም። በእቅዴ መሰረት ቀጥታ ወደ ስራ መግባት ነው።

ስለ ክለብ ቆይታዎቻቸው?

መጀመርያ ተጫዋች እያለሁ ነው ማሰልጠን የጀመርከት። ዲላ ከተማ እያለሁ በአንድ አጋጣሚ አሰልጣኙ ተሰናበተ እና እኔና ሀብታሙ ገብረሃና የሚባል ተጫዋች ክለቡን እንድናሰለጥን ተወስኖ ክለቡን ተረከብን። ከዛ እየተጫወትኩ ማሰልጠን ጀመርኩ። ብዙ ነገር መማርም ጀምሬ ራሴን ለማሻሻልም ብዙ መፃሐፍት አነብ ነበር።
በዛ መሀልም በ1988 በፕሮጀክት ስራዎች ሰርተናል። በዲላ በርካታ ዓመታት ሰርቻለው። ከዛ ከብዙ ቆይታ በኃላ በ2011 በጥር ወር ወደ ደቡብ ፓሊስ አመራሁ። በዛኑም ዓመት ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊግ አሳድገነዋል።

ስለ መጨረሻ ክለባቸው ወላይታ ድቻ ቆይታ?

በወላይታ ድቻ ጥሩ ቆይታ ነበረኝ። ወላይታ ድቻን የለቀኩበት መንገድ እነሱ እንጂ እኔ አላውቀውም ፤ እኔ በወቅቱ ምንም የተበላሸ ነገር አልነበረም ነው የምለው። ያው ሁሉም ነገር በቀጣሪዎች ነው የሚወሰነው። ቻምፒዮን ሆነህም ትለያያለህ። ግን ያለፈ ስለ ሆነ ብዙም አያስፈልግም። እግር ኳስ ሁሉም ነገሩ ወደ ፊት ነው ፤ አስተሳሰቡም የአጨዋወት እንቅስቃሴውም ወደፊት ነው ስለዚህ ስላለፈ ነገር ብዙ አይጨንቀኝም። ቀጣይ ምን ልስራ የሚለው ነው ወሳኙ ነገር።

መጨረሻ…

ለማሰልጠን ዝግጁ ነኝ ማንኛውንም ክለብ ማሰልጠን እችላለሁ ፤ ማንኛውም ክለብ በእኔ እምነት ካለው ዝግጁ ነኝ።