በእግር ኳስ ውስጥ የሚያጋጥሙ የተለያዩ የጤና እከሎችን በምንበለከትበት በሶከር ሜዲካል ዓምድ የዛሬው ትኩረታችን የሚሆነው ድንገተኛ የሆነ የልብ ድካም እንዴት መከላከል እና ማከም እንደሚቻል ነው፡፡
የልብ ህመም ተዘውትረው ከሚታዩ እና ከፍተኛ ጉዳት ከሚያስከትሉ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በተፈጥሮም ሆነ ከሚያደርጓቸው ጫና የበዛበት እንቅስቃሴ አንጻር ለእነዚህ ህመሞች ተጋላጭ ናቸው፡፡ በቅርብ ጊዜ በአውሮፓ ሀገራት ውድድር ወቅት በዴንማርካዊው አማካይ ክርስቲያን ኤሪክሰን ላይ የደረሰው ጉዳትም ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
በእግር ኳስ ሜዳ ውስጥ የሚያጋጥሙ ድንገተኛ የሞት አደጋዎች መንስኤ የሆነው አንዱ ድንገተኛ የልብ ድካም ( Sudden Cardiac Arrest) ነው፡፡ ይህ እንዳያጋጥም ቅድመ ምርመራዎች ( Screening) የሚያስፈልግ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ህመሙ ካጋጠመ በኋላ የሚደረጉ እርዳታዎች ማለትም Cardiopulmonary Resuscitation ( CPR) እና Automated External Defibrillator ( AED) ህይወትን ከማትረፍ በኩል ያላቸው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡
እንደዚህ ያለው ህመም በአብዛኛው ጊዜ በእንቅስቃሴ ወቅት የሚያጋጥም ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ የልብ ምት መዛባት (arrythmia) የሚያጋጥመው በዚህን ወቀት በመሆኑ ነው፡፡
የድንገተኛ የልብ ህመም መንስኤ የልብ መዋቅራዊ (structural) እና ኤሌክትሪካዊ መስተጋብር ላይ በሚኖር ችግር አልያም መዛባት ምክንያት ነው፡፡
የልብ ቅድመ ምርመራ ( Cardiovascular Screening )
የልብ ቅድመ ምርመራ ዋንኛው አላማ ለድንገተኛ የልብ ህመም የሚያጋልጥ የጤና ዕከሎችን አስቀድሞ መለየት እና ማወቅ ነው፡፡ ይህንንም ለማደረግ የእግር ኳስ የበላይ አካል የሆነው FIFA Pre-competition Medical Assessment የተሰኘ የምርመራ ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡ በዚህም ምርመራ መሰረት የተጫዋቾች የህክምና ታሪክ ፤ የቤተሰብ የህክምና ታሪክ እና የተለያዩ የልብ ምርመራዎች የሚደረጉ ይሆናል፡፡
– ECG ምርመራ የተጫዋችነት ዘመን ሀ ተብሎ ሲጀመር መደረግ ያለበት ምርመራ ሲሆን ከዛም በኋላ በየዓመቱ ሊቀጥል ይገባዋል፡፡
– የልብ አልትራሳውንድ ( Echocardiography) በምርመራ ወቀት ችግር የታየባቸውን ተጫዋቾች የበለጠ ለመመርመር ይጠቅማል፡፡ ይህም በልብ ስፔሻሊሰት የሚሰራ ሲሆን በአንድ ተጫዋች የውድድር ዘመን ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ እንዲሰራ ይመከራል፡፡
– ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆኑ ተጫዋቾች በእንቅስቃሴ ላይ የሚደረግ የECG ምርመራ እንዲደረግላቸው ይመከራል፡፡
ከ60-80 % የሚሆኑ ድንገተኛ የልብ ህመም የሚያጋጥማቸው ተጫዋቾች ከህመሙ መከሰት በፊት ምንም አይነት ምልክት የማያሳዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን በቀሪዎቹ ላይ የሚከተሉት ምልክቶች ይስተዋላሉ፡- ድንገተኛ ራስን መሳት፤ በእንቅስቃሴ ላይ የሚያጋጥም የደረት ህመም፤ ምክንያቱ ያልታወቀ የሰውነት መንቀጥቀጥ፤ የትንፋሽ ማጠር እና በቶሎ መድከም ናቸው፡፡
በቤተሰባቸው ውስጥ የታወቀ የልብ ህመም ካለ አልያም ከ50 በታች ዕድሜ ውስጥ በድንገት ህይወቱ ያለፈ የቅርብ ዘመድ ያላቸው ተጫዋቾች ቅርብ የሆነ ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል፡፡
ድንገተኛ የልብ መድከም በሚያጋጥመበት ወቅት በቶሎ ምላሽን ለመስጠት መመሪያዎችን ያቀፈ ጽሁፍ በልምምድ ቦታዎችም ሆነ ውድድር በሚደረግባቸው ስፍራዎች ሊዘጋጁ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ የድንገተኛ ምላሽ መመሪያዎች የተለያዩ ነገሮችን በውስጣቸው ያቀፉ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል ለህክምና አባላቱ ቀጣይነት ያለው ስልጠና መስጠት ፤ በአጭር ደቂቃ ውስጥ መሳሪያዎችን ( Defibrillator) የመጠቀም ክህሎት ፤ ወደ ህክምና ስፍራ በቶሎ ተጫዋቾችን መውሰድ እና የመሳሰሉት ተካተውበታል፡፡