የአሠልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 4-0 ሀምበሪቾ ዱራሜ

አራት ለምንም ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ለማጥቃት ነበር አስበን ወደ ሜዳ የገባነው። እንደተመለከታችሁትም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ብዙ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ነበሩን። የእነርሱንም ባህሪ ለመጠቀም የሚያስችል አጨዋወት ለመጠቀም ሞክረናል። በዚህም ተሳክቶልናል። ከዚህ በፊት የነበረው ቡድን ኳስ መስርቶ ብቻ ነበር የሚጫወተው። ኳስ መመስረቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ፊት የመሄድ አቅም ያስፈልገው ነበር። ይሄንንም ነገር ነበር ለተጫዋቾቹ የነገርኳቸው። የነገርኳቸውንም ተግባራዊ አድርገውት አሸንፈን ወጥተናል።

በእናንተ ጥንካሬ ነው ወይስ በተጋጣሚ ቡድን ድክመት ያሸነፋችሁበት የጎል መጠን የሰፋው?

ተጋጣሚያችን ቀላል ቡድን አይደለም። ጠንካራ ቡድን ነው። ለተቃራኒያችንም ክብር አለን። ግን የእኛ ተጫዋቾች በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ ነው ያደረጉት። ኳስም ስንይዝ ቶሎ ወደ እነርሱ ሜዳ እንገባ ነበር። ውጤቱም የሰፋው ጥሩ ስለተንቀሳቀስን እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ስለምንሄድ ነው።

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች?

ቀጣይ ጨዋታዎችንም አሸንፈን መውጣት እና በፕሪምየር ሊጉ መቆየት ነው ፍላጎታችን። ስለዚህ ቀጣይ ጨዋታም በዚሁ መንገድ እንጫወታለን።

ግርማ ታደሠ – ሀምበሪቾ ዱራሜ

ስለጨዋታው?

በጨዋታው ከመጀመሪያው ጀምሮ የተጋጣሚ ቡድን ኳስ ይዞ የመጫወት አቅም በጣም የተሻለ ስለነበር በዛ ነበር ተዘጋጅተን የመጣነው። ትንሽ አጥብበን ጨዋታውን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገን ነበር። ነገር ግን እነሱ ከእኛ በጣም የተሻሉ ናቸው። በሥነ-ልቦና ባላቸው አቅም የእኛን ስህተቶች በመጠቀም በጣም የተሻሉ ነበሩ። በቅድሚያ የገቡብን ሁለት ጎሎች የእኛን ቡድን አውርዶታል ብዬ አስባለሁ። በሁለተኛው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ ለማስተካከል ሞክረናል። ነገር ግን ያው ያገኙትን አጋጣሚዎች አላባከኑም። በአግባቡ ተጠቅመውታል ፤ በልጠውን ነው ያሸነፉት።

በሰፋ የግብ ልዩነት ስለመሸነፋቸው?

የተጋጣሚ ቡድን ጥንካሬ ነው አልልልም። የእኛ የመከላከል አቅም በጣም አነስተኛ ነው። ቡድኑ ላይ የነበሩ ወሳኝ ተጫዋቾች አለመኖራቸው አስቸጋሪ አድርጎብናል። ለማስተካከል ብዙ ያልተጠቀምናቸውን ተጫዋቾች ነው እየተጠቀምን ያለነው ፤ ያ ትንሽ ተፅዕኖ አምጥቶብናል። ለማስተካከል ሞክረናል ከመጀመሪያው ጨዋታ ሁለተኛው የተሻለ ነው። ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ ነው ማለት ለእኛም አስቸጋሪ ነበር።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች?

ሦስቱንም ጨዋታዎች በአግባቡ እንጫወታለን። ይህ መድረክ ለተጫዋቾቹም ለቡድኑም ምቹ ነው እና የተሻለ ነገር እንዲሰሩ ነው የምናስበው። አሁንም ቡድን እየሰራን ነው የምንመጣው። ተጫዋቾቹ ያላቸውን አቅም አውጥተው እንዲጫወቱ በሚገባ አዘጋጅተን ነው የምንመጣው። ካለፈው ጨዋታ የአሁኑ የተሻለ ነው ቀጣዩ ደግሞ ከአሁኑ ይሻላል የሚል ዕምነት አለኝ።