ለሁለት ቀን እረፍት የተሰጠው የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብ በዛሬው ዕለት ወደ ልምምድ ተመልሷል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ በሚዘጋጀው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ከሰኔ 4 ጀምሮ ዝግጅቱን ሲያደርግ ነበር። የሴካፋ ውድድር የመጀመሪያ ጊዜ ከመገፋቱ በፊት ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ወደ ባህር ዳር አቅንቶ የነበረው ልዑካኑም ሰኞ የሴካፋ ውድድር መራዘም መሰማቱን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደርጓል። የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱም ለ25ቱ ተጫዋቾች የሁለት ቀን የእረፍት ጊዜ ሰጥተው ነበር።
በአሠልጣኙ የተሰጠው የእረፍት ጊዜ ትናንት ካበቃ በኋላ ሁሉም ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልህዕቀት ማዕከል ተሰባስበዋል። ተጫዋቾቹ ማለዳ ላይ በማዕከሉ ከተገኙ በኋላ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ እንዲያመሩ ተደርጎ ልምምድ መሰራቱ ታውቋል። ሶከር ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ቡድኑ ባገኘው መረጃ ሁሉም ተጫዋቾች (25) በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ብሔራዊ ቡድኑም ከዚህ በኋላ በቀን አንድ ጊዜ መቀመጫውን ባደረገበት የካፍ የልህዕቀት ማዕከል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ልምምዱን እየሰራ ቆይቶ የሴካፋ ውድድር ሊጀመር (ሐምሌ 10) አንድ ሳምንት ሲቀረው ወደ ባህር ዳር እንደሚያቀና ተነግሯል።
በተያያዘ ዜና የብሔራዊ ቡድኑ አባላት በነገው ዕለት የኮቪድ-19 ክትባት እንደሚወስዱ ተጠቁሟል። ተጫዋቾቹ ጠዋት ላይ ክትባቱን ከወሰዱ በኋላም ከሰዓት እረፍት እንደሚያደርጉ እና ልምምዳቸውን ቅዳሜ ረፋድ እንደሚቀጥሉ ሰምተናል።