የሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ሊደረግ ነው

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሴቶች ክልል ክለቦች ሻምፒዮናን ለመጀመርያ ጊዜ ሊያካሂድ ተዘጋጅቷል፡፡

በስሩ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን በሚል ያለፉትን ዓመታት ሲያወዳድር የቆየው ፌዴሬሽኑ አሁን ደግሞ የውድድሩን አድማስ በማስፋት ሦስተኛ የውድድር ዕርከን በቅርቡ ለማድረግ መዘጋጀቱን የፌዴሬሽኑ የውድድር ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ከሆነ ክለቦች እና ከተማ አስተዳደሮች የሴት ቡድኖች ዘንድሮ የማምጣት እና የማሳተፍ አቅሙ ካላቸው ባሉት ቡድኖች ብቻ የክልል ክለቦች የሴቶች ሻምፒዮና በሚል ይደረጋል። ለዚህም ውድድር ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ከፀደቀ በኃላ በቀጣይ በሚገለፅ ከተማ ውድድሩን እንደሚደረግም ሰምተናል፡፡

በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ ሆነው በደረጃ የሚያጠናቅቁ ክለቦች ምናልባትም አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የሚያድጉ ይሆናል፡፡

በተያያዘ እስከ አሁን የውድድር ቦታ እና ቀን ያልተገለፀው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ክልሎች የተወዳዳሪ ክለቦችን ቁጥር ከአራት ወደ አምስት እንዲያሳድጉ የተገለፀ ሲሆን የምዝገባውም ገንዘብ 50 ሺህ ብር መሆኑን አረጋግጠናል፡፡