ሪፖርት | ኮልፌ ቀራኒዮ ወደ ድል ተመልሷል

የትግራይ ክልል ቡድኖችን የፕሪምየር ሊግ ቦታ ለማሟላት በሚደረገው ውድድር ኮልፌ ቀራኒዮ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-0 በመርታት ነጥቡን በጊዜያዊነት ከመሪው አዳማ ጋር አስተካክሏል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጅማ ላይ ባሳካው ድል የተጠቀመበትን አሰላለፍ ሳይቀይር ጨዋታውን ሲጀምር ኮልፌ ቀራኒዮ ከአዳማው ሽንፈት ግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ኃይማኖት አዲሱን በአዲስኪዳን ኪዳነማርያም ቦታ ተክቷል።

ለኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቦታ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታውን በጥሩ ፉክክር ጀምረዋል። በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተሻለ ሁኔታ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቀርበው የታዩ ሲሆን በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግን ኮልፌዎች የበላይነቱን በመውሰድ ከፍ ባለ ጫና ለማጥቃት ሞክረዋል። ቡድኑ 18ኛው ደቂቃ ላይ ባደረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራም የቀኝ መስመር አማካዩ አንዋር ዱላ ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባት የመታውን ዘሪሁን ታደለ አድኖበት አጥቂው ሀቢብ ከማል የተተፋውን ኳስ ለማስቆጠር ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል። የኮልፌዎች የበላይነት እስከ ውሀ ዕረፍቱ ቆይቶ ቢታይም ቡድኑ ከካስ ቁጥጥር ብልጫው ውጪ ሌላ ከባድ ሙከራ ሳያደርግ ቀርቷል።

ጨዋታው ለውሀ ዕረፍት ተቋርጦ ሲቀጥል ኤሌክትሪኮች እየደረሰባቸው የነበረውን ጫና መቀነስ ችለዋል። ነገር ግን አጋማሹ እስኪቃረብ ድረስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጠንካራ ሙከራ አልተመለከትንም። ወደ መጨረሻው ግን አጨዋወታቸው ላይ ቀጥተኛነት እየተነበበባቸው የመጡት ኤሌክትሪኮች ኢላማቸውን ባይጠብቁም ግብ መሆን የሚችሉ ሁለት ዕድሎችን አምክነዋል። 42ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ እንዳለ ዘውገ ከግራ መስመር በተሻገረ ኳስ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ለማስቆጠር ቢሞክርም የኮልፌው መሀል ተከላካይ ፉዐድ ነስሩ ተደርቦ አውጥቶበታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከሳሙኤል ታየ በረጅሙ ተልኮ በድጋሚ ከግራ መስመር በአቤል ታሪኩ የተሻማውን ኳስ ደግሞ የቡድኑ አጥቂ አደም አባስ ነፃ ሆኖ በግንባሩ ቢገጭም ኳሱ ወደ ላይ ተነስቶበታል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ኤሌክትሪኮች የበላይነቱን በመውሰድ ጀምረዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ ከደሳለኝ ወርቁ የረጅም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ጥሩ ዕድል አግኝተው ያልተጠቀሙት ኮልፌዎችም በሂደት በእንቅስቃሴ መመጣጠናቸው አልቀረም። 59ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከአቤል የተቀበለውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ተጫዋች አልፎ ሞክሮ ለጥቂት ለወጣበትን ከባድ ሙከራም ኮልፌዎች በግብ ምላሽ ሰጥተዋል። 61ኛው ደቂቃ ላይ በሰነዘሩት ፈጣን ጥቃት ተመስገን ዘዉዱ በቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል።

ከግቡ በኋላ የጨዋታው ግለት ከፍ ብሎ እና ጉሽሚያዎች እየተደጋገሙ ፉክክሩ ቀጥሏል። ኤሌክትሪኮች ኳስ ይዘው ባልተረጋጋ አካኋን ክፍተት ፍለጋ በኮልፌ ሜዳ ላይ ቢቆዩም የተጋጣሚያቸው የማልሶ ማጥቃት አካሄድ ይበልጥ አስፈሪ እና ሳጥን ውስጥ የሚደርስ ነበር። 82ኛው ደቂቃ ላይም ከኤሌክትሪኮች በተነጠቀ አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ግብ አስቆጣሪው ብሩክ በግራ መስመር እየነዳ የወሰደውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ አሰልፎለት ተቀይሮ የገባው አብዱሰላም የሱፍ ግብ አድርጎታል። በቀሩት ደቂቃዎች ኤሌክትሪኮች በተመሳሳይ አኳኋን ለማጥቃት ቢጥሩም በግራ መስመር ተቀይሮ የገባው ፀጋ ደርቤ ካደረጋቸው ሁለት ሙከራዎች ሌላ ልዩነቱን ማጥበብ ሳይችሉ ጨዋታው በኮልፌ አሸናፊነት ተጠናቋል።