ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር የሟሟያ ውድድሩን የመጀመሪያ ድል አሳክቷል

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የንጋቱ ገብረሥላሴ ብቸኛ ጎል ጅማ ሀምበርቾን 1-0 እንዲረታ አስችላለች።

ጅማ አባ ጅፋር ከኤሌክትሪኩ ሽንፈት ባደረገው አንድ ለውጥ ሳዲቅ ሴቾን በራሂም ኦስማኖ ምትክ አሰልፏል። በሀምበርቾ ዱራሜ በኩል ደግሞ ብሩክ ኤልያስ እና ሮቦት ሰለሎ ወደ አሰላለፍ መጥተው አመረላ ደልታታ እና አላዛር አድማሱ ከወልቂጤው ጨዋታ መልስ አርፈዋል።

በአመዛኙ በመሀል ሜዳ ላይ በነበረ ፍትጊያ ያለፈው የመጀመሪያ አጋማሽ የግብ ዕድሎች ተደጋግመው አልታዩበትም። አንፃራዊ ብልጫ የነበራቸው ጅማ አባ ጅፋሮች በሀምበርቾ ሜዳ ላይ ብዙ ደቂቃ ቢያሳልፉም የመጨረሻ ቅብብሎቻቸው ስኬት የወረደ መሆን ተፅዕኗቸውን ዝቅ አድርጎታል። ተመስገን ደረሰ እና ፕሪንስ ዋንጎ ከረጅም ቅጣት ምት ያደረጓቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችም በእሸቱ አጪሶ የተመለሱ ነበሩ።

መልሶ ማጥቃትን መሰረት ያደረጉት ሀምበርቾዎችም የሚፈልጓቸው አጋጣሚዎች አልፎ አልፎ ሲፈጠሩ ቢታዩም በማጥቃት ወቅት ከወገብ በላይ የነበራቸው የቁጥር መሳሳት የብሩክ ኤልያስን ፍጥነት ለመጠቀም መሞከር ላይ ብቻ እንዲወሰኑ አድርጓቸዋል። 30ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም በቀለ ከርቀት ካደረገው ደካማ ሙከራ ውጪም ሌላ የግብ ዕድል አልፈጠሩም። የአጋማሹ ጥሩ ሙከራ የታየውም 45ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ፕሪንስ ከማዕዘን ተሻምቶ የተመለሰን ኳስ ሲወርድ አግኝቶ በቀጥታ አክርሮ መትቶ እሸቱ በድጋሚ አድኖበታል።

ከዕረፍት መልስ ጅማዎች ወዲያው ጎል አግኝተዋል። 46ኛው ደቂቃ ላይ በሳዲቅ ሴቾ የተተካው ራሂም ኦስማኖ ሳጥን ውስጥ ያመቻቸውን ኳስ ባልተለመደ መልኩ ግብ አቅራቢያ የተገኘው ንጋቱ ገብረስላሴ ማስቆጠር ችሏል። ሀምበርቾዎች ግቡ ከመቆጠሩ በፊት አርቢትሩ ኳስ ነክተዋል በሚል ቅሬታ ቢያሰሙም ጎሉ ፀድቆ ጨዋታው ቀጥሏል። ተቀያሪው ኦስማኖ 53ኛው ደቂቃ ላይም ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ሀምበርቾ ዱራሜዎች ምላሽ ለመስጠት ወደ ፊት ገፍቶ የማጥቃት ፍላጎት እየታየባቸው ቢቀጥልም አስፈሪ እንቅስቃሴ ማድረግ ግን አልቻሉም።

ቀሪዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ደካማ እንቅስቃሴ ያስመለከቱን ነበሩ። ሀምበርቾዎች ተደጋጋሚ የቆሙ ኳሶች ዕድሎችን መጠቀም ሳይችሉ ሲቀሩ ጅማዎችም በተጋጣሚ የግብ ክልል ላይ የግብ ዕድል መፍጠር የሚያስችል መናበብ ሳይታይባቸው ግን ደግሞ መሪነታቸውን ማስጠበቁ ሆኖላቸው ጨዋታውን በድል ጨርሰዋል።

ያጋሩ