በኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቅ ስም ያለው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ደጉ ደበበ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የዘንድሮ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከክለቡ ወላይታ ድቻ ጋር ሆኖ ድንቅ ዓመትን አሳልፏል። የቀድሞ የአርባምንጭ ጨርቃጨርቅ (እስከ 1996) እና ቅዱስ ጊዮርጊስ (እስከ 2010) ተጫዋች ምንም እንኳን አንጋፋ ከሚባሉ እና በአሁኑ ሰዓት በሊጉ ላይ እየተጫወቱ ካሉ ተጫዋቾች መካከል በግንባር ቀደምትነት ቢጠቀስም እድሜ ሳይበግረው በጥሩ ብቃት እየተጫወተ ይገኛል። በዘንድሮ የሊጉ ውድድር ላይ 1673 ደቂቃዎችን የተጫወተው ደጉ ከሰሞኑ “ጫማውን ሰቀለ” የሚሉ ወሬዎች በርከት ብለውበት እየተሰሙ ይገኛሉ። ይሄንን ጉዳይ በተመለከተም ሶከር ኢትዮጵያ ራሱ ተጫዋቹን አናግራ ተከታዩን ምላሽ ይዛለች።
“የስፖርት ቤተሰቡ እንደተመለከተው ዘንድሮ በጣም ጥሩ ዓመት ከክለቤ ወላይታ ድቻ ጋር አሳልፌያለሁ። በቀጣይ ዓመትም ይሄንን ብቃቴን እንደማስቀጥል አስባለሁ። መሥራት እየቻልኩ ለምን መጫወት አቆማለሁ? እንዳልኩት ጥሩ ጊዜ ዘንድሮ ነበረኝ። መሥራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ስደርስ አቅሜ ራሱ ይነግረኛል። ስለዚህ ‘ደጉ ጫማ ሰቅሏል’ እየተባለ የሚወራው ወሬ ሀሰት ነው። ወደ ስልጠናው ዓለምም የምገባበት ጊዜ ገና ነው።”
2006 ላይ በራሱ ፍቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን ያገለለው ደጉ ከዚህ በኋላ ለስንት ዓመት ለመጫወት ሀሳብ አለህ ብለን ለጠየቅነው ጥያቄ “በዚህ ዓመት ውስጥ እግርኳስ መጫወት አቆማለሁ ብዬ አልወሰንኩም። ይሄንንም ማሰብ ትንሽ የሚከብድ ይመስለኛል። እግርኳስ የአደባባይ ላይ ሥራ ስለሆነ አቅሜን አይቼ ነው የምወስነው። ስለዚህ እግርኳስ መጫወት ለጥቅም ብቻ ሳይሆን እየወደድኩት የምሰራው ሙያ ስለሆነ ገደብ ማስቀመጥ ከባድ ነው። እንደገለፅኩት ፊት ለፊት የሚታይ ነገር ስለሆነ አቅም ሲከዳኝ ብቻ ነው የማቆመው።” የሚል ምላሹን ሰጥቶናል።