የአሰልጣኞች አስተያየት | ኮልፌ ቀራኒዮ 0-3 ወልቂጤ ከተማ

ወልቂጤ ከተማ ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ኮልፌ ቀራኒዮን ከረታበት ጨዋታ በመቀጠል ሁለቱም አሰልጣኞች የድህረ ጨዋታ ሀሳባቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

“ጨዋታው እንዳያችሁት ከባድ ነበር፡፡ምክንያቱም ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ይዘው የሚጫወቱ ቡድኖች ስለሆኑ። በአጠቃላይ ግን ከጨዋታ በስተጀርባ እዚህ ድረስ የመጡ ደጋፊዎቻችን ማመስገን እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ከፕሪምየር ሊግ ወጥተናል ብለው በነበሩበት ሰዓት ይሄን ውጤት በማሳካታችን በተለይ ከጎኔ የነበረውን የቡድን መሪ ሌሎችም አመራሮችም አመሰግናለሁ። ጨዋታው እንዳያችሁት ለተመልካች እይታ በጣም የሚያምር፤ ጎል ጋር ቶሎ የሚደረስበት ስለነበረበት በተጨማሪም ቡድኑ እንደዛ በሆነበት ሰዓት ተረክቤ እዚህ ደረጃ ላይ ማድረሴ እኔም ደስተኛ ነኝ። ለደጋፊው ደስታ ነው፡፡”

ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበራቸው ብልጫ

” እረፍት ላይ ያወራነው ነገር ተጋጣሚያችን ኳስ ስለሚጫወቱ የመሐል ቁጥራችንን ለማብዛት ፈልገን ነበር፡፡ መስመር ላይ አሜ እና አቡበከር ሳኒን መልሰን ተጫውተው እንዲገቡ አደረግን። ያም ውጤታማ ሆኖ ግባችንን መቷል፡፡

መሐመድኑር ንማ – ኮልፌ ቀራኒዮ

ምስጋና

በቅድሚያ ፈጣሪዬን ማመስገን ፈልጋለሁ። ለዚህ ደረጃ ያበቃን አላህን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። በመቀጠል ተጫዋቾቼን በጥረታቸው እዚህ ደረጃ ስለመጡ እነሱንም ማመስገን እፈልጋለሁ። የክለቡ ኃላፊዎች እዚሁ ሀዋሳ አካባቢ ያሉ ደጋፊዎች የስፖርቱ ቤተሰብ እንደ አጠቃላይ ይሄን ዕድል ደግሞ ለፈጠረው ለአወዳዳሪው አካል ማመስገን እፈልጋለሁ።

ስለጨዋታው እና ውድድሩ

የዛሬው ጨዋታ አጀማመራችን በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ዕድልም አግኝተን ነበር። ያንን ዕድል ብንጠቀም ኖሮ ጨዋታው ይቀየር ነበር። ተቆጣጥረናቸው ነበር። በአጠቃላይ የተቃራኒን ቡድን አጨዋወት በደንብ ስላየን ሙሉ በሙሉ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥረነው ነበር፡፡ዕድል ስናገኝ ያንን ስንስት ወደ መረበሽ አይነት ገቡ። ያው ልምድም ስለሌላቸው ከዛ ጫና መውጣት አልቻሉም። ሲሳት ተስፋ ወደ መቁረጥ ገቡ። በሁለተኛው አጋማሽ የልምድ ማነሶች ነው የጎዱን።

የዓመቱ ጉዞ እና አመራሩ

እነሱ (አመራሩ) አእስካሁን ባመጣነው ውጤት ደስተኞች ናቸው። ምክንያቱም ከከፍተኛ ሊግ ነው የመጣነው። እየተወዳደርን ያለነው ከፕሪምየር ሊጎች ጋር ነው፡፡ ከከፍተኛ ሊግ የመጡትን ተፎካካሪዎች አሸንፈናል። ፕሪምየር ሊግ ያሉትን ነው መቋቋም ያቃተን፤ ይሄም የልምድ ማነስ ነው፡፡ ልምድ ነው፤ መቼ መፍጠን መቼ መቀዝቀዝ እንደዳለባቸው አለማወቃቸው ነው ችግር የሆነብን። እኔ ግን ባሉት ነገሮች ሁሉ ደስ ብሎኛል፡፡