የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 1-0 ሀምበርቾ ዱራሜ

ሶከር ኢትዮጵያ ከደቂቃዎች በፊት ተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የአሰልጣኞችን አስተያየት ተቀብላለች።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው

ጨዋታው ብዙ መልክ ነበረው። አንደኛ ከሽንፈት ነው የመጣነው። ሁለተኛ ጠዋት መሸናነፍ ስለነበር በሰንጠረዡ ተጠግተን መቆየታችንን እንፈልገው ነበር። እርግጥ ነው ጫና ነበረብን ውጤት ለማስጠበቅ ተጨንቀን እንጫወት ስለነበር። ሙሉ ለሙሉ በፈለግነው መንገድ ሄዷል ባንልም በውጤት ደረጃ ግን ጥሩ ሆኖልናል ማለት እቻለለሁ።

ጎል አካባቢ ስለሚታየው የመናበብ ችግር

ውጤት ከማስጠበቅ አንፃር ከነበረብን ጫና ጎል አካባቢ አለመረጋጋቶች ይታያሉ። ያንን አስተካክለን መምጣት አለብን። አስተካክለን ቀጣዮቹን ጨዋታዎች አሸንፈን ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን።

አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ – ሀምበርቾ ዱራሜ

በግቡ ላይ ስለነበራችው ቅሬታ

ዳኛው ሥራው ህግ ማስከበር ነው። ጎሉ ሲገባ ግን ህግ ተጥሶ ነው የገባው። ከዛ አንፃር ነው ጥያቄ ያነሳነው። ጎሉ ሲገባ ዳኛው ስለነካ እና ስለመቻቸው ህጉ እንደገና ማስጀመር አለበት ነው የሚለው። ከህግ አኳያ ውሳኔው ግልፅ ስላልነበር ነው እኛንም ሴሜታዊ ያደረገን። ያው በዛ ጎል ተሸንፈናል።

ስለጨዋታው

ከጨዋታ ጨዋታ የተሻሻለ ነገር ይታያል። መጀመሪያ የተቸገርባቸው ነገሮች እየተስተካከሉ ነው። ይህን ጨዋታም እናሸንፋለን የሚል ዕምነት ይዘን ነው የገባናው። ነገር ግን ሜዳ ላይ የተፈጠረው ነገር እኛን ጎድቶናል።

ወደፊት ሲሄድ ቡድኑ ስለሚታይበት መሳሳት

ባሉን ተጫዋቾች ላይ ተመርኩዘን ነው እየተጫወትን ያለነው። የተሻለ የመንጠቅ አቅም የነበራቸው ተጫዋቾችን ማጣታችን ክፍተት ፈጥሮብናል። ያን ችግር ለመቅረፍ ዘግይተው ወደ ተቃራኒ ሜዳ ሲገቡ የመድረስ አቅማቸው አነስተኛ ነው። ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ ለማስተካከል ሞክረናል። ግን በዛ ልክ ተጫዋቾች ብቁ አልሆኑልንም። በጥንቃቄ አጨዋወት ውስጥ ቆይተን ያገኘነውን አጋጣሚ ለመጠቀም ነው ጥረት ያደረግነው። የተወሰነ መሻሻል አለ ግን አጥጋቢ ነው የሚል ሀሳብ የለኝም።