የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ አዳማ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማን አገናኝቶ ያለግብ ተጠናቋል።
ከድል ከተመለሱት ሁለቱ ቡድኖች ውስጥ አዳማ ከተማ አብዲሳ ጀማልን በማማዱ ኩሊባሊ ምትክ የተጠቀመበትን ብቸኛ ቅያሪ ሲያደርግ ወልቂጤ ከተማ ግን የአሰላለፍ ለውጥን አለማድረግ መርጧል።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረጉት እንቅስቃሴ የፉክክር መጠኑ ከፍ ብሎ ቢታይም የመጨረሻ የግብ ዕድሎች ግን ብበሚፈለገው መጠን አልተስተዋሉበትም። 35ኛው ደቂቃ ላይ በዳማ በኩል ከጀሚል ያዕቆብ የእጅ ውርወራ የተነሳውን ኳስ አብዲሳ ጀማል ከርቀት አክርሮ ለመምታት ያደረገው ጥረት በጀማል ጣሰው ከመዳኑ በቀርም ግብ ጠባቂዎችን የሚፈትኑ የግብ ዕድሎች ሲፈጠሩ አልታየም። በአመዛኙ ጉሽሚያ የተበራከተበት የቡድኖቹ ፍልሚያ መሀል ሜዳ ላይ ተወስኖ ሲቀር ቡድኖቹ በተመሳሳይ አኳኋን ኳስ መስርተው ለመውጣት የሚያደርጓቸው ጥረቶች ሲቆራረጡ ታይቷል። በዚህም አጋማሹ ያለግብ እና ያለከባድ ሙከራዎች እንዲገባደድ ሆኗል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በሙከራ ረገድ ተሻሽሎ በሁለቱም ግቦች በኩል ጥሩ የግብ አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ መታየት ጀምሯል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ አህመድ ከአብዲሳ ከግራ አቅጣጫ የደረሰውን ኳስ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ሞክሮ ወደ ላይ ተነስቶበታል። ከሦስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ በወልቂጤ በኩል አብዱለሪም ወርቁ ከቀኝ መስመር ያሻማውን እና ረመዳን የሱፍ ሳጥን ውስጥ ያመቻቸለትን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ወደ ግብ ቢልከውም ሙከራው ወደ ውጪ ወጥቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ የአዳማው በላይ አባይነህ እና የወልቂጤው አቡበከር ሳኒ ያገኟቸውን ጥሩ ዕድሎች ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ከኢላማ ውጪ ሆኗል።
በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል ከወገብ በላይ የተደረጉ ቅያሪዎች ሌሎች የግብ ዕድሎችን ይዘው መጥተዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ አብዲሳ ጀማል ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው እንዲሁም
83ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ተሻገር ከርቀት ያደረገው ጠንካራ ሙከራ በሳኩምባ ካማራ ተመልሶ አህመድ ሁሴን ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ የሆነባቸው አጋጣሚዎች በዚህ ውስጥ የሚነሱ ናቸው። 88ኛው ደቂቃ ላይም አሚን ነስሩ በጨረፈው ኳስ ተቀይሮ የገባው ሔኖክ አየለ ሌላ ግልፅ አጋጣሚ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም ሳኩምባ አውጥቶበታል። ከዕረፍት በፊት ሙከራ አልባ የነበረው ጨዋታም በሁለተኛ አጋማሽ ግልፅ ዕድሎች በተደጋጋሚ ቢታይበትም ግብ ሳይቆጠር ሊጠናቀቅ የግድ ሆኗል።