የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-0 አዳማ ከተማ

የማሟያው ውድድር ሦስተኛ ቀን የማሳረጊያ ጨዋታ መጠናቀቅ ተከትሎ አሰልጣኞች ይህንን ብለዋል።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለውጤቱ

ያው እንደተመለከታችሁት ነው መናገርም አያስፈልግም ሁለት ነጥብ ጥለናል።

ስለተሻረው ኳስ

እኔ እዚህ ጋር ማንንም ተወቃሽ አላደርግም። ምክንያቱም የጨዋታው አንድ ገፅ ነው። ፍርዱን ለተመልካች ትቻለሁ ስለዳኝነት ምንም ማለት አልፈልግም።

ቡድኑ ላይ ስላለው መሻሻል

ከዚህ በፊት ቡድኑ ጎል ጋር በመድረስ ረገድ ያለውን አቅም እና አሁን ያለውን ተመልክታቸኋል። ስለዚህ ይሄ ነው ይሄ ነው ብል ትርጉም የለውም። ደጋፊውም ሕዝቡም የተመለከተው ጨዋታ ነው። ቡድኑ ከፍተኛ ለውጥ አለው ፤ እያጠቃ ነው የሚጫወተው። ሲያጠቃ የሰው ቁጥር እያበዛን ነው የምንጫወተው። ሜዳ ላይ የነበሩት ተጫዋቾችም የአጥቂ ባህሪ ነው የነበራቸው ስለዚህ በአጠቃላይ በነበረው ነገር ደስተኛ ነኝ።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – አዳማ ከተማ

ስለቡድኑ የመከላከል መሻሻል

ቡድን ለመስራት ጊዜ ያስፈልጋል። በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ወደ ሀዋሳ ስንመጣ መሻሻሎች ነበሩ። ከስብስብ አንፃር ፊት ላይ ነው የምንቸገረው እንጂ ከኋላ ክፍላችን ላይ በደንብ ሰርተናል። እስካሁን ጎሎች ያልገቡብንም ያንን መሰረት አድርገን ስለሰራን ነው። ከዛ ውጪ በምናገኛቸው ኳሶች ነው በመልሶ ማጥቃት መሄድ የምናስበው። መጠቀም አልቻልንም እንጂ ብዙ ዕድል አግኝተናል። በመከላከሉ ረገድ ግን ብዙ ልፋት ቢጠይቅም ለማጠናከር ሞክረናል መሻሻሎችም አሉ።

ስለአጨራረስ ችግር

አንድ የፊት አጥቂ ያለን አብዲሳ ነው። አብዲሳም ከጉዳት ነው የመጣው። ቢሆንም ግን የተሻለ ጎል ጋር ደርሷል። የመጨረስ ችግር ይታይበታል ሆኖም ግን ዓመቱን ሙሉ ጫናው እሱ ላይ ስለነበር ነው ጉዳትም የደረሰበት። መስመር ላይም ከታችኛው ቡድን ተጫዋቾች አምጥተን እየተጠቀምን ነው። በጥቅሉ ፊት ላይ ካለን የስብስብ ጥበት አንፃር በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር የሞከርነው።