በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚደረገው የሴካፋ ውድድር ላይ ከቀጠናው ሀገራት በተጨማሪ በተጋባዥነት እንደምትሳተፍ የገለፀችው ሀገር ከውድድሩ ውጪ ሆናለች።
ከሐምሌ 10 ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ የሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ውድድር አስራ አንድ የቀጠናው እና አንድ ተጋባዥ ሀገራትን በማሳተፍ እንደሚደረግ ሲነገር ቆይቷል። በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉ የሚጠበቁት ብሔራዊ ቡድኖችም ለተጫዋቾቻቸው ጥሪ እያቀረቡ ዝግጅት ማድረግ ይዘዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲሱ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ዧን-ክሎድ ሎቦኮ አማካኝነት ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርቦ የነበረው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቡድን ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚጀመረው የሴካፋ ውድድር ላይ እንደማይሳተፍ ተረጋግጧል።
ከሀገር ውስጥ ተጫዋቾች በተጨማሪ ከቻይና፣ ቤልጂየም፣ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ እና ሞሮኮ ሊጎች የተመረጡ ተጫዋቾች ይዞ ልምምድ ሲሰራ የነበረው ብሔራዊ ቡድኑም ምክንያቱ በግልፅ ባልታወቀ ሁኔታ ራሱን ከውድድሩ ውጪ ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በተያያዘ ለመረጃዎች እምብዛም ክፍት ያልሆነው የቀጠናው እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (ሴካፋ) እስካሁን (ፅሁፉን እስካዘጋጀንበት ሰዓት) እርግጥ ያለውን የውድድሩ ተሳታፊዎችን ቁጥር ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዳላሳወቀ ተገልጿል።