በሀገራችን በሚደረገው የሴካፋ ውድድር ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ልምምዱን አጠናክሮ መስራት ቀጥሏል።
ሀገራችን ለአምስተኛ ጊዜ የምታስተናግደው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ውድድር ላይ የሚሳተፈው የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብ ከሰኔ 4 ጀምሮ ልምምዱን እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል። ባሳለፍነው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የሴካፋ ውድድር የሚጀመርበት ቀን ለሁለት ሳምንት መገፋቱ ከተሰማ በኋላ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለተጫዋቾች የሁለት ቀን እረፍት ሰጥተው ዳግም ከሀሙስ ጀምሮ ልምምድ መስራት ይዘዋል። በዛሬው ዕለትም ልዑካን ቡድኑ ከ4:25 ጀምሮ መደበኛ ልምምዱን ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ አከናውኗል።
ለሁለት ሰዓት በቆየው የቡድኑ የልምምድ ጊዜ የግብ ዘቡ ምንተስኖት አሎ እና ሀብታሙ ተከስተ ከሌሎች የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ጋር ሆነው ልምምድ ሲሰሩ አልተመለከትንም። ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገው ማጣራትም ምንተስኖት አሎ ባልተገለፀ የግል ጉዳይ የአማካይ መስመር ተጫዋቹ ሀብታሙ ተከስተ ደግሞ በህመም ምክንያት የዛሬው ልምምድ እንዳለፋቸው አውቀናል።
በቅድሚያም በዛሬው ልምምድ የተገኙት 23 ተጫዋቾች ከኳስ ጋር የተገናኘ ማፍታቻ ካደረጉ በኋላ የግል የቴክኒክ ብቃታቸውን ሊያጎለብት የሚችል ሥራ እንዲሰሩ ተደርጓል። በተለያየ መዋቅር የተቀረፀው ለየት ያለው የልምምድ አሠጣጥ ከተከናወነ በኋላ ደግሞ አሠልጣኝ ውበቱ እና ረዳቶቹ አራት የተከላካይ እና አራት የአጥቂ ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በግማሽ ሜዳ እያፈራረቁ በተቃራኒ ሲያሰሩ አስተውለናል። በተለይ በዚህ የልምምድ አሠጣጥ ላይ የመስመር ተከላካዮቹ (ኃይሌ፣ ዩሃንስ፣ አማኑኤል እና ሀይለሚካኤል) ሜዳውን አስፍተው እንዲጫወቱ ትዕዛዝ ሲሰጥ አይተናል። እየተፈራረቁ የተጫወቱት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ደግሞ ተከላካዮች ኳስ መስርተው እንዳይወጡ ተጭነው እንዲጫወቱ እና ግብ የማስቆጠሪያ ክፍተቶችን ለማግኘት የሚያስችላቸውን መፍትሄ እንዲያገኙ ምክር ሲሰለገስ አስተውለናል። የግብ ጠባቂ አሠልጣኙ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው ፅዮን መርዕድን እና ፋሲል ገብረሚካኤልን የቅልጥፍና፣ የጊዜ አጠባበቅ እና የውሳኔ አሠጣጥ ልምምዶችን ሲያሰሩ ተመልክተናል።
ከላይ የተጠቀሱት ልምምዶች ከተሰሩ በኋላ ቡድኑ ለሁለት ተከፍሎ በግማሽ ሜዳ መደበኛ ጨዋታ እንዲከውን ተደርጓል። በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ተጫዋቾች ዘለግ ያለውን ጊዜ ከኳስ ጋር እንዲያሳልፉ ተደርጎ ነበር። ከዚህ ውጪ አራቱም የሜዳ ክፍሎች ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ያማከለ እንቅስቃሴ እንዲከናወን አሠልጣኞቹ ሲመክሩ አይተናል። በተጨማሪም ተጫዋቾች በጨዋታው መሐል በሚገኙ የቅጣት እና የመዓዘን ምቶች ላይ የቡድን ሥራ የታከለበት የቆመ ኳስ አጠቃቀም ሲለማመዱ ለማስተዋል ችለናል። የዛሬው የልምምድ መርሐ-ግብርም 6:25 ሲል ተጠናቆ ተጫዋቾች በስነ-ምግብ ባለሙያው ዳንኤል ክብረት የተዘጋጀላቸውን ፈሳች ወስደው ከሜዳ ወጥተዋል። በተያያዘ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ የሚሰሩትን ልምምድ የቪዲዮ አናሊስት ባለሙያው ኤልሻዳይ ቤኬማ በካሜራ እንዲቀረፅ ሲያደርግ ታዝበናል።
በቀጣዮቹ ቀናትም በቀን አንድ ጊዜ ልምምዱን እየሰራ የሚቀጥለው ብሔራዊ ቡድኑ የሴካፋ ውድድር ከሚጀመርበት ቀን (ሐምሌ 10) አንድ ሳምንት አስቀድሞ ወደ ባህር ዳር እንደሚያቀና ሰምተናል።