የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቀጣዩ ዓመት በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከ3 በላይ የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ማስፈረም እንደማይቻል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ፌዴሬሽኑ እንዳስታወቀው ቀደም ሲል በነበረው የውጭ ሀገር ተጫዋቾች የዝውውር መመሪያ መሠረት አንድ ክለብ እስከ አምስት ድረስ የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች የሚያስፈርምበት አሰራር ከ2014 የውድድር ዘመን ጀምሮ ቁጥሩን በመቀነስ 3 ተጫዋቾች ብቻ ማስፈረም የሚችሉ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም በከፍተኛ እና በ1ኛ ሊግ ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦች ምንም ዓይነት የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ማስፈረም የማይቻሉ መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን በ2012 የውድድር ዘመን ጅማሮ ላይ የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸውም ግብ ጠባቂዎች ይቅሩ? ወይንስ በሊጉ ላይ ይቀጥሉ? በተጨማሪነትም የውጪ ሀገር ተጫዋቾችን ቁጥር በአንድ ክለብ ውስጥ ከሚፈቀደው የቁጥር ብዛት (አምሰት) ይቀንስ? ወይንስ ባለው ይቀጥል? በሚለው ጉዳይ ላይ ሰነድ አዘጋጅቶ በተለይ ለፕሪምየር ሊግ ክለቦች ከዛም በከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ላይ ላሉ ክለቦች ጥያቄ መላኩ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ክለቦች የተላከላቸውን የመጠይቅ ሰነድ በመላኩ ረገድ ደካማ ሆነው በመገኘታቸው ፌዴሬሽኑ በያዝነው ወር ይሄንን የቤት ሥራ ለመስራት ሲገደድ እንደነበር ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በተጨማሪም የሀገሪቱን እግርኳስ በበላይነት የሚመራው አካል የውጪ ሀገር ግብ ጠባቂዎችን ለማስቀረት የጊዜ ሒደት ስለሚያስፈልግ እንዲሁም በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ክለቦች በመኖራቸው ለጊዜው ይቅሩ የሚለውን ጉዳይ ማስቀረቱን ሰምተናል፡፡