የፕሪምየር ሊግ ማሟያ ውድድር – የነገ ጨዋታዎች ዳሰሳ

በ2014ቱ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ የትግራይ ክልል ክለቦች ካልተሳተፉ በቦታቸው የሚካፈሉትን ለመወሰን የሚደረገው ውድድር የአራተኛ ዙር ጨዋታዎችን እንዲህ ዳሰናቸዋል።

ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ ከ ጅማ አባ ጅፋር (03፡30)

የረፋዱ ጨዋታ ባሳለፍነው ቅዳሜ በሦስተኛው ዙር ድል ማጣጣም የቻሉትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኝ ይሆናል። ከአዳማ ከተማው የሰፊ ልዩነት ሽንፈት ጥሩ በሚባል ብቃት እና በኤሌክትሪክ ላይ ባስመዘገበው ድል ያገገመው ኮልፌ ይህን ጨዋታም ካሸነፈ በዘጠኝ ነጥቦች ከላይ የመቀመጥ ዕድልን ያገኛል። የውድድሩን የመጀመሪያ ድል በሀምበርቾ ላይ ያሳከው ጅማም የዚህን ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ሰባት ደርሶ በሊጉ የመቆየት ዕድሉን እንዲያሰፋ በር ይከፍትለታል።

ኮልፌ ቀራኒዮ በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ እጅግ ተሻሽሎ ታይቷል። የተጋጣሚን ብልጫ በእንቅስቃሴ አክስሞ ጨዋታን በራሱ ቅኝት የማስኬድ እና ኳስ ተቆጣጥሮ ዕድሎችን መፍጠር ላይ ጥሩ አፈፃፀም ነበረው። ይህን ጥንካሬውን ለነገው ጨዋታ ይዞ መቅረብ እና በስብስቡ ላይ የሚታየውን ተነሳሽነት ይዞ መቀጠልም የአሰልጣኝ መሀመድ ኑር ዋነኛ ትኩረት ይመስላል። ጅማ በሀምበርቾው ድሉ የውድድሩን ደካማ ቡድን የገጠመ ቢሆንም በጨዋታው ላይ ያሳየው በድፍረት ወደ ፊት ገፍቶ ለመጫወት ያለው ተነሳሽነት በጠንካራ ጎኑ የሚታይ ነው። ነገር ግን ነገ ለኳስ ቁጥጥር ትልቅ ትኩረት ከሚሰጥ ተጋጣሚ ጋር መገናኘቱ ሲታሰብ ጥንቃቄ አዘል የመሆን እና ለመልሶ ማጥቃት ትኩረት መስጠት ከቡድኑ ይጠበቃል። ከዚህም አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የአጥቂዎቻቸው ፍጥነት እና ውሳኔ አሰጣጥ ጎልብቶ እንዲቀርብ ይጠብቃሉ፡፡

ሀምበርቾ ዱራሜ ከ አዳማ ከተማ (07፡00)

የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በእስካሁኑ የውድድሩ ሂደት ከላይ እና ከታች የተቀመጡት ቡድኖችን የሚያገናኝ ይሆናል። ከወልቂጤ ጋር ጠንካራ ፉክክር አድርጎ ነጥብ የተጋራው አዳማ ነጥቡን አስር አድርሶ ለከርሞው በሊጉ የመታየት ዕድሉን በእጅጉ የሚያሰፋበት ዕድል ይኖራል። በተቃራኒው እስካሁን ምንም ነጥብ የሌለው ሀምበርቾ በውድድሩ ስኬታማ የመሆን ዕድሉ ጨርሶ እንዳይጨልም በዚህ ጨዋታ አንዳች ልዩነት መፍጠር የግድ ይለዋል።

ሀምበርቾ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻሎችን ቢያሳይም አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት እንደሚያዳግተው የጅማው ጨዋታ አሳይቶን አልፋል። በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ከወገብ በታች ባለው ቅርፁ ላይ መጠቀሙ ወደ ፊት ሲሄድ በተጨዋቾች የግል ፍጥነት ላይ በቻ እንዲመረኮዝ እና በቁጥር ጥቂት ተጫዋቾችን በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ማድረሱ ተጋጣሚዎች በቀላሉ እንዲከላከሉት በር ሲከፍት ታይቷል። እነዚህ ነጥቦች በቡድኑ በኩል ካልተስተካከሉ የነገው ጨዋታም ቀላል የሚሆንለት አይመስልም። ከወልቂጤ ከተማ ከባድ ፍልሚያ የገጠመው አዳማ ከዓመቱ ጉዞው የተሻለ በራስ መተማመን የሚታይበት ቡድን ቢሆንም በግብ ፊት የሚሳቱት የቡድኑ የማጥቃት ሂደቶች ግን ትልቁ ድክመቶቹ ናቸው። በዚህም በነገው ጨዋታ አጥቂዎቹ የተሻለ የአፈፃፀም ብቃት እንዲኖራቸው የግድ ይላል። ከዚህ በተለየ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ 42 ግቦችን ያስተናገደው ቡድን እስካሁን በዚህ ውድድር ምንም ግብ ያልተቆጠረበት መሆኑ ለሀምበርቾ ጥቃት በቀላሉ እንደማይፈታ የሚጠቁም ነው።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወልቂጤ ከተማ (10፡00)

በመሀላቸው የሁለት ነጥብ ልዩነት ኖሮ ሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ከዕለቱ ፍልሚያዎች በንፅፅር ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠውን ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከሦስት ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያሳካው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድሩ የመጣለትን የሊጉ ምልሰት ዕድል ፈር ለማስያዝ ይህ ጨዋታ እጅግ በጣም ወሳኙ ይሆናል። ከተጋጣሚው የተሻለ ሁኔታ ላይ የሚገኘው ወልቂጤ ከታማም ድል ቀንቶት የነጥብ ስብስቡን ስምንት ማድረስ ከቻለ የመጨረሻ ጨዋታውን ያለብዙ ጫና የማድረግ ዕድሉ የሰፋ ይሆንለታል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በኮልፌው ጨዋታ ሁለት አጋማሾች በጥሩ ጉበት ጨዋታውን ቢጀምርም በሂዱት ከጨዋታ ቅኝት መውጣቱ እና የቅብብል ስህተቶችን መስራቱ ለሽንፈት ዳርጎታል። በነገው ከባድ ፍልሚያም በዋነኛነት የተጫዋቾችን ትኩረት ከፍ ማድረግ እና ቡድኑ ያለጫና በእርጋታ ጨዋታውን ማከነዋን እንዲችል ማድረግ የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ዋነኛ የቤት ስራ ይሆናል። የቡድኑ የኳስ ምስረታ ሂደት ዝግ ማለት እና የቅብብሎቹ በተደጋጋሚ መቋረጥም ተመሳሳይ አጨዋወት ለሚከተለው ወልቂጤ ከተማ እጅ እንዲሰጥ ሊያደርገው ይችላል። ወልቂጤ ከተማ ዓመቱን እንዳሳለፈበት ሁኔታ አሁንም የአጨራረስ ችግሩ አብሮት እንዳለ በአዳማው ጨዋታ በተደጋጋሚ መመልከት ችለናል። ወጣ ገባ የሚለው የወትሮው የቡድኑ አጥቂዎች ብቃትም በዚህ ጨዋታ ላይ ተስተካክሎ መቅረብ ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ ከተጋጣሚው የተሻለ ኳስ የመያዝ ብቃቱ ጨዋታውን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ሁለተኛው የሜዳ አጋማሽ ላይ ለመቆየት ዕድል እንደሚሰጠው ሲታሰብ መጠነኛ መሻሻል ያሳየው የኋላ ክፍሉ አልፎ አልፎ ከመስመር የሚነሳውን የመልሶ ማጥቃት ባህሪ የተላበሰ የኤሌክትሪክን የማጥቃት አካሄድ መግታት ይጠበቅበታል።