በሴካፋ ውድድር ላይ ለመካፈል በዝግጅት ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ተጫውቷል።
41ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ በባህር ዳር ከተማ ከሐምሌ 10 ጀምሮ እንደሚደረግ ሲጠበቅ የኢትዮጵያ ከ 23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን ማድረግ ቀጥሏል። 23 ተጫዋቾችን ይዞ ቡድኑ በዛሬው ዕለትም ቃሊቲ አካባቢ በሚገኘው የመድን ሜዳ ከኢትዮጵያ መድን ስብስብ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርጓል።
የወዳጅነት ጨዋታው ሁለት የአንድ ሰዓት ክፍለ ጊዜዎች የነበሩት ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ ሁለት የተለያዩ ቡድኖችን ተጠቅሟል። በመጀመሪያው ቡድን ፂዮን መርዕድን በግብ ጠባቂነት ኃይሌ ገብረትንሳይ ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ መናፍ ዐወል ፣ ዮሃንስ ሴጌቦ በተከላካይነት ሀብታሙ ተከስተ ፣ አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ እና ዊልያም ሰለሞን በአማካይነት እንዲሁም ቸርነት ጉግሳ ፣ አቡበከር ናስር እና መስፍን ታፈሰ በአጥቂነት ለሁለት 30 ደቂቃዎች ተጫውተዋል። በዚህም መስፍን ታፈሰ ከርቀት፤ ዊሊያም ሰለሞን ደግሞ ከቸርነት ጉግሳ ጋር አንድ ሁለት በመቀባበል ባስቆጠሯቸው ጎሎች ክፍለ ጊዜውን በ 2-0 የበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል።
በሁለተኛው 60 ደቂቃ በብሔራዊ ቡድኑ በኩል ግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ፋሲል ገብረሚካኤል በተከላካይነት አማኑኤል እንዳለ ፣ እያሱ ለገሰ ፣ ፀጋሰው ድማሙ እና ዱሬሳ ሹቢሳ መሀል ላይ በረከት ወልዴ ፣ ወንድምአገኝ ኃይሉ እና ዳዊት ተፈራ እንዲሁም ከፊት ሙኸዲን ሙሳ ፣ ሥንታየሁ መንግሥቱ እና ብሩክ በየነ ተሰልፈው ተጫውተዋል። ይህኛው የጨዋታ አጋማሽ ፀጋሰው ድመሙ በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠረው ግብ መድን 1-0 መጨረስ ችሏል። በአቋም መለኪያው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በጥቅሉ ከሰበታ ከተማው ኃይለሚካኤል አደፍርስ ውጪ የተቀሩትን 22 ተጫዋቾች ተጠቅመዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ እና አንድ አንድ የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች የታደሙቡት የወዳጅነት ጨዋታም በብሔራዊ ቡድኑ አጠቃላይ የ2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ብሔራዊ ቡድኑ የአዲስ አበባ ዝግጅቱን እስከ ሳምንቱ ፍፃሜ በማድረግ በቀጣዩ ሰኞ ውድድሩ ወደሚደረግበት የባህር ዳር ከተማ እንደሚጓዝ ይጠበቃል።