ሲዳማ ቡና ሁለት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

ከሁለት ቀናት በፊት ቡድኑን ለማጠናከር ወደ ዝውውር ገበያው ጎራ ያለው ሲዳማ ቡና ሁለት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡

የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌን ውል ለማራዘም በሒደት ላይ የሚገኘው ክለቡ ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ተጫዋች ዝውውር ገበያው በመግባት ግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆን በሁለት ዓመት ውል ወደ ክለቡ ያመጣ ሲሆን አሁን ደግሞ የትግራይ ክልል ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ ካልተሳተፉ እነሱን ለመተካት በሀዋሳ ሲደረግ የነበረውን ውድድር ሲከታተሉ የነበሩት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ሁለት ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊጉ ኮልፌ ቀራኒዮ ተመልክተው ወደ ቡድናቸው አካተዋል፡፡

አንዋር ዱላ ወደ ሲዳማ ያመራው የቡድኑ ሁለተኛ ፈራሚ ነው፡፡ በኮልፌ ቀራኒዮ አመርቂ የውድድር ዓመትን ያሳለፈው እና በማሟያውም ውድድር ድንቅ አቅሙን ሲያሳይ ነበረው የፊት እና የመስመር አጥቂው ለሲዳማ ቡና የማጥቃት አማራጭን ለማስፋት በሁለት ዓመት የውል ዕድሜ ክለቡን ለመቀላቀል ተስማምቷል፡፡

የክለቡ ሦስተኛ ፈራሚ ተጫዋች ብሩክ ሙሉጌታ ነው፡፡ በመስመር እና በአጥቂነት በኮልፌ ቀራኒዮ ያሳለፈው ፈጣኑ ተጫዋች በማሟያው ውድድር ላይ አስደናቂ ብቃቱን ሲያሳይ ነበረ ሲሆን በቀጣይ ዓመት ደግሞ በሲዳማ ቡና መለያ በፕሪምየር ሊጉ ለመድመቅ ቡድኑን ተቀላቅሏል፡፡

ያጋሩ