ሀዲያ ሆሳዕና በዛሬው ዕለት የአሠልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል

ከቀናት በፊት ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ለማምራት ተስማምተው የነበሩት አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረት የነብሮቹ አዲስ አሰልጣኝ መሆናቸው በዛሬው ዕለት እርግጥ ሆኗል።

በ2013 የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ ጠንካራ ጅማሮ አድርጎ የነበረው ሆሳዕና ከበርካታ ውዝግብ ጋር ታጅቦ በምክትሉ ኢያሱ መርሐፅድቅ መሪነት አራተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል። አዲሱን የውድድር ዓመት ደግሞ በወጣቱ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረት ለመጀመር የሁለት ዓመት ኮንትራት መፈራረማቸው ታውቋል።

ከ1990ወቹ ጅማሮ አንስቶ በሦስት የተለያዩ ጊዜያት ሀዋሳ ከተማን በተጫዋችነት ያገለገሉት ሙሉጌታ ምኅረት በ2008 እግርኳስን አቁመው በሀዋሳ እና ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝነት ከሰሩ በኋላ ዓምና ከተቋረጠበት የውድድር ዓመት ጀምሮ ነበር ላለፉት 18 ወራት በዋና አሰልጣኝነት የሀዋሳ ከተማን የመሩት።

አሰልጣኙ ከሰሞኑ ውላቸው መጠናቀቁን ተከትሎ ድርድር እያደረጉ የሰነበቱበት ሀድያ ሆሳዕናን በዋና አሰልጣኝነት በዛሬው ዕለት ተቀላቅለዋል፡፡ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ማዶሮ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁትም “አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በታዳጊ ላይ የተሻለ የመስራት አቅም ስላለው እና ክለቡን ዘንድሮ የተሻለ ተፎካካሪ ያደርጋል ብለን በማሰብ ነው የቀጠርነው።” ብለዋል፡፡

ኃላፊው አያይዘው በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ክለቡ የተነሳበትን የክፍያ ችግር ዘንድሮ ሙሉ በሙሉ በማስተካከል የክለቡን ስም ለማደስ እንደተዘጋጁ ነግረውናል፡፡