የአዲስ አበባ ስታዲየም የዕድሳት ሥራ በይፋ ተጀምሯል

ለዘመናት ያለበቂ የማሻሻያ ስራዎች አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም የዕድሳት ሥራ በዛሬው ዕለት መጀመሩን የኢፊዲሪ ስፖርት ኮሚሽን አስታውቋል።

የኢፊዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ከሁለት ሳምንታት በፊት ለወራት ከዘለቀ የጨረታ ሒደት በኃላ ከተመረጠው ፍሬንድስ ኢንጅነሪንግ ኃ.የተ. የግል ኩባንያ ጋር በገባው የውል ስምምነት መሠረት ስራው በዛሬው ዕለት የተጀመረ ሲሆን በዕድሳቱ የመጀመርያ ምዕራፍ ከሚከናወኑ ሥራዎች መካከል የመጫወቻ ሣሩን ሙሉ ለሙሉ የመቀየር ፣ ለተጋጣሚ ቡድን አባላት የሚሆኑ የመልበሻ እና የመታጠቢያ ክፍሎች እንዲሁም ለእድምተኞች የሚሆኑ መፀዳጃ ቤቶችን ጨምሮ የስታዲየሙን የኤሌክትሪክ እና የሳኒተሪ መሰረተ ልማቶችን የማሻሻል ሥራዎች እንደተካተቱበት ተገልጿል።

በዛሬው ዕለት ሥራው የተጀመረው የዚህ እድሜ ጠገብ ስታዲየም የማሻሻያ ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ በእግርኳሱ ተፅዕኗዋ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ለመጣችው አዲስ አበባ ከተማ በጎ ዜና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።