በወልቂጤ ከተማ ሦሰት ለምንም አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።
ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ
ስለ ጨዋታው?
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ትንሽ ጭንቀት ነበረብም። ምክንያቱም ጨዋታው ወሳኝ ጨዋታችን ነበር። ግን ጨዋታው ላይ ጥሩ ብልጫ ነበረን። ኳስ ከሚቆጣጠር ክለብ ጋር ነበር የተጫወትነው። ግን እንዳያችሁት ኳሱን በደንብ ይዘን ተጫውተናል። በአጠቃላይ ብልጫውን ወስደን ተጫውተናል።
ስለ ቡድኑ ጠንካራ ጎን?
እንደሚታወቀው የቡድኑ ደካማ ጎን ወደ ፊት የመሄድ እና ግብ የማስቆጠር ችግር ነበር። እንደታየው ግን ይህ ክፍተት ተስተካክሏል። ተጫዋቾቼ ከኳስ ጋር ነው የሚጫወቱት። ሲያጠቁም ሆነ ሲከላከሉ በጋራ ነው። ከዚህ ውጪ ኳሱን በትልቅ ብልጫ መቆጣጠር መቻላችን ጠንካራ ጎናችን ነው።
ስለ ቀጣዩ ወሳኝ ጨዋታ?
የሚቀጥለውም ጨዋታ ለእኛ ወሳኝ ነው። ቀጣይ ተጋጣሚያችን ኮልፌ ስድስት ነጥብ ነው ያለው። ስለዚህ ጨዋታው ከባድ ነው። ጨዋታውንም በዛሬው መንፈስ በመቅረብ በፕሪምየር ሊጉ ለመቅረት እንሞክራለን።
ኃይሉ አድማሱ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ (ምክትል አሠልጣኝ)
ስለ ጨዋታው?
ጨዋታው ጥሩ ነበር። ግን እንደ አጀማመራችን አልቀጠልንም። አጀማመራችን ጥሩ ነበር። ቢሆንም ጎሎች ተቆጠሩብን። ከዛ በኋላ ደግሞ ጨዋታውን በምንፈልገው መንገድ መምራት ተሳነን። ጎሎች ቢቆጠሩም ቅያሪዎችን አድርገን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገናል። በአጠቃላይ በሁለታችንም በኩል የነበረው የኳስ ፍሰት ጥሩ ነበር። ግን እኛ በምናስበው መንገድ ጨዋታው አልሄደልንም።
ሦስት ጎል ስለማስተናገዳቸው እና አንድም ጎል ስላለማግባታቸው?
ዛሬ ከወትሮው በተለይ የወልቂጤዎች የተከላካይ ክፍል ጠጠር ያለ ነበር። የእኛም ተጫዋቾች በየሦስት ቀኑ ጨዋታ ስለሚያደርጉ ድካም ነበረባቸው። እነዚህ ነገሮች ይመስለኛል ውጤቱ እንዲሰፋ ያደረገው። ቀድሜም እንዳልኩት ውጤቱ ያስፈልገን ነበር። የገቡብን ጎሎች ደግሞ ጫና አሳደሩብን።