በዘንድሮ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማን እያገለገለ የነበረውን ግብ ጠባቂ ህይወት ቀጥፏል የተባለው ተከሳሽ የፍርድ ውሳኔ እንደተላለፈበት ዳጉ ጆርናል ዘግቧል።
በሚያዚያ ወር አዳማ ላይ ሲከናወን በነበረው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ በሀዋሳ ከተማ ስብስብ ውስጥ የነበረው ግብ ጠባቂው አቤል አየነ የውድድሩ ፍፃሜ ሰሞን በአዳማ ከተማ አስተዳደር ደንበላ ክፍለ ከተማ ኢሬቻ ቀበሌ ልዩ ቦታው ቦርጋን መኝታ ቤት አካባቢ ያልተጠበቀ ድርጊት ተፈፅሞ በእግርኳሱ አሳዛኝ ታሪክ መከሰቱ ይታወሳል። በዚህም የግብ ዘቡ አቤል አየነ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሚያዚያ 16 ቀን 2013 ምሽት ላይ ለመዝናናት ይወጣሉ። ጓደኛማቾቹ ወደ አንድ ምሽት ክለብ ለመግባት ሲሞክሩ የክለቡ ጠባቂ (ጋርድ) የሆነው ዳግም ጀማል የተባለ ግለሰብ ‘በነጠላ ጫማ ወደ ውስጥ መግባት አይቻልም’ ብሎ ይከለክላቸዋል፡፡ ክልከላውን ተከትሎ በጊዜው ጓደኛማቾቹ ወደ ሌላ ስፍራ ለማምራት ወስነው ይንቀሳቀሳሉ። ሆኖም ከለሌቱ ስምንት ሰዓት ላይ ወደ መዝናኛ ስፍራው እንዳይገቡ የተከለከሉት ጓደኛማቾች በጎዳና ላይ በድጋሚ ከዳግም ጀማል ጋር ይገናኛሉ። ዳግምም ‘በዚህ በምሽት መንገድ ላይ ምን ትሰራላችሁ? ለምንስ ታመሻላችሁ’ ሲል ይጠይቃቸዋል። በጥያቄው መነሻነት የተነሳው ንግግር የኋላ ኋላ የከረረ ጭቅጭቅ እና ፀብ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗቸው አደጋ ይከሰታል።
በጊዜው ተከሳሽ ንዴቱን መቆጣጠር አቅቶት ይዞ በነበረው ጩቤ የግል ተበዳይ አቤል በመውጋት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገ ሲሆን በፈፀመው ወንጀል በመፀፀት በአቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በመጓዝ እጅ ሰጥቷል። የአዳማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ባሳለፈው ውሳኔም ተከሳሽን ጥፋተኛ በማለት በ19 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የብስራት ሬድዮ ጋዜጠኛ ስምኦን ደረጄ ከአዳማ ከተማ አስተዳድር ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ መናገራቸውን ዘግቧል።