ነገ የሚከፈተውን የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በተመለከተ የፊፋ የቲ ኤም ኤስ ማኔጀር እና የፊፋ ኮንታክት ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ዘውድነሽ ይርዳው ለሶከር ኢትዮጵያ በዝውውር መስኮቱ ሊታወቁ የሚገባቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል።
ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2014 የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዙር የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ መቼ እንደሆነ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል። በዚህም የመጀመሪያው ዙር የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ ከነገ ሐምሌ 1 ጀምሮ ለ84 ቀናት (መስከረም 19) እንደሚከናወን ተገልጿል። ነገ በይፋ የሚከፈተውን የዝውውር መስኮት በተመለከተ ሶከር ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፊፋ የቲ ኤም ኤስ ማኔጀር እና የፊፋ ኮንታክት ባለሙያ የሆኑትን ወ/ሮ ዘውድነሽ ይርዳውን አግኝታ ጥያቄዎችን አቅርባቸዋለች። ከባለሙያዋ ጋር የተደረገው ቆይታም እንደሚከተለው ቀርቧል።
ከትናንት በስትያ መሰጠት የጀመረ ስልጠና አለ። ይህ ስልጠናው ምን አይነት ይዘት ነበረው? ምንን ታሳቢ ተደርጎ ነው የተሰጠውስ?
ስልጠናው ለሁለት ቀን የተዘጋጀ ነበር። ትናንት እና ዛሬ ተከናውኖ ተጠናቋል። ግን አዲስ ስልጠና አይደለም። ሁሌ በየዓመቱ የሚሰጥ ነው። ስልጠናው ለፕሪምየር ሊግ ክለብ የአይቲ (ቲ ኤም ኤስ) ባለሙያዎች የተዘጋጀ ነበር። ለነባሮቹ እንደ ሪፍሬሽመንት ለአዲሶቹ (መከላከያ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ) ደግሞ የግንዛቤ መስጫ ስልጠና ነው። እንዳልኩት የሁለት ቀን ስልጠና ነው። በዋናነትም ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ተነስተውበታል። በትናንት ውሎ በተጫዋቾች ዝውውር ጉዳይ ላይ ነው ስልጠና የሰጠነው። ይህ የሀገር ውስጥም ሆነ የሀገር ውጪን ዝውውር ያካተተ ነው። ሁለቱም ዝውውሮች በሲስተም የሚያልፍ ስለሆነ እሱን እንዲያውቁት ነው የተደረገው። የዛሬው ውሎ ደግሞ የተጫዋች ምዝገባን የተመለከተ ነበር። ሁሉም የሊጉ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን በፊፋ ኮኔክት ሲስተም መመዝገብ እንዳለባቸው አስረድተናል። ማንኛውም ከ10 ዓመት በላይ ያለ ተጫዋች በዚህ ሲስተም እንዲመዘገብ እናደርጋለን። ከዛ ተጫዋቹ የፊፋ መታወቂያ (አይ ዲ) ይኖረዋል። ይህ ደግሞ የተጫዋቾችን እድሜ ለመቆጣጠር ይረዳል።
ይህ ፊፋ ኮኔክት የሚለውን ሲስተም ዓምና ነበር የጀመርነው። የተወሰነም ሰርተንበታል። ግን አንዳንድ ክለቦች ትኩረት ሰጥተውት አልሰሩበትም ነበር። አሁን ግን በአስገዳጅ ሁኔታ ከህክምና ኮሚቴ ጋር አንድ ላይ በመሆን እንዲሰራበት እናደርጋለን። ሲስተሙ ላይ የህክምና ሁኔታ ያስፈልጋል። ስለዚህ ይህም ሲሟላ ነው ሲስተሙ ላይ ምዝገባ የሚከናወነው። ይህ ካልሆነ ግን ምዝገባውም ሆነ ዝውውሩ አይፀድቅም። ይሄንንም ለክለቦቹ በደንብ ነግረናል። ለሁለት ቀንም ስልጠናው የቆየው ጉዳዩን በደንብ እንዲያውቁት ነው።
በስልጠናው ላይ ሁሉም የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ተገኝተዋል?
አብዛኞቹ ክለቦች ተገኝተዋል። ዘንድሮ ወደ ሊጉ ያደጉት አዲስ አበባ፣ መከላከያ እና አርባምንጭም ነበሩ። ግን በዚህ የሁለት ቀን ስልጠና ወልቂጤ ከተማ፣ ጅማ አባጅፋር እና ወላይታ ድቻዎች አልተገኙም። ለምን እንዳልመጡም አናውቅም።
በዚህ የዝውውር መስኮት ሊታወቁ የሚገባቸው የተለየዩ ወይም አዳዲስ ደንብ እና ህግጋቶች ይኖሩ ይሆን?
ብዙ የተለየ ነገር የለውም። ያለውን ለማስታወስ ግን አንድ ተጫዋች ዝውውር ለማድረግ ወደ እኛ ሲመጣ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጉታል። አንደኛው ከመጣበት ክለብ መልቀቂያ ይዞ መምጣት አለበት። ሁለተኛው ማንነቱን የሚገልፅ መታወቂያ አልያም የልደት ካርድ ያስፈልገዋል። ሦስተኛ እና የመጨረሻው አዲስ ከገባበት ክለብ ጋር የተፈራረመበት ውል ነው። እነዚህ ነጥቦች በፊትም ነበሩ። ግን ለምሳሌ መልቀቂያ ብዙ ጊዜ ተጫዋቾች ትክክለኛውን አያመጡም ነበር። ወይ የአምናውን ኮፒ ያመጣሉ አልያም ክለቤ አልሰጠኝም ይሉ ነበር። ከዘንድሮ ጀምሮ ግን ይሄ አይሰራል። የትኛውም ተጫዋች መልቀቂያውን ከክለቡ ማምጣት አለበት። ክለብ አልሰጥም ካለው ፌዴሬሽን አመልክቶ በህጉ መሠረት ፌዴሬሽኑ ክለቡን ይጠይቃል። ተጫዋቹ በምን ምክንያት መልቀቂያ እንዳልተሰጠውም ለእኛ ያብራራል ማለት ነው።
ምናልባት አዲሱ እና ኮስተር የምንልበት ህግ የህክምና እና የኢንሹራንስ ጉዳይ ነው። ከዚህ በፊት በአስገዳጅ ሁኔታ ተጫዋቾች የህክምና ማረጋገጫ እንዲያመጡ አይጠየቁም ነበር። ከዚህ በኋላ ግን ይህ ህግ አለ። ከዚህ በተጨማሪ ክለቦች ለሚያስፈርሙት ተጫዋች ኢንሹራንስ መግባት ይጠበቅባቸዋል። ይሄም በፊት ደንቡ ላይ ነበር ግን ተግባራዊ አይደረግም ነበር። ከነገ ጀምሮም የክለብ ሥራ-አስኪያጆችን ስለምናገኝ ጉዳዩን በደንብ እንነግራቸዋለን። ከዚህ ውጪ ግን አዲስ ነገር የለም። ያሉትን ግን ኮስተር ብለን ተግባራዊ እናስደርጋለን።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽም የትኛውም ክለብ ከሦስት በላይ የውጪ ተጫዋች እንዳያስፈርም ወስኗል። የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር ገደብን አስመልክቶ ከሦሰት በላይ ኮንትራት ያላቸው ተጫዋቾችን የያዙ ክለቦች ካሉስ..?
ውል ያለው ተጫዋች ውሉን ይጨርሳል። አሁን የወጣው ህግ አዲስ ለሚያስፈርሙ ክለቦች ነው። ውል ማቋረጥ ስለማይቻል አንድ ክለብ አራት ውል ያላቸው የውጪ ተጫዋቾችን ቢይዝ አዲስ ማስፈረም አይችልም። ግን እነሱን ይዞ ቀጣይ ዓመት ይወዳደራል። እንዳልኩት ውል ማቋረጥ ስለማይቻል ውል ያለው ይቀጥላል። አለበለዚያ ፊፋ ይቀጣል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከሦሰት በላይ ውል ያላቸው የውጪ ተጫዋቾችን የያዘ ክለብ አለ?
ውሉን ማየት ያስፈልጋል። ምናልባት ነገ ሲስተሙ ውስጥ ገብቼ ይሄንን ላጣራ እችላለሁ። እኛም ይሄንን መለየት ስላለብን ከነገ ጀምሮ የመለየት ስራ እሰራለሁ።
በመጨረሻ ከኢንተርሚዲየሪዎች ጋር እየተነሳ ያለውን ልዩነት ግልፅ አድርጊልኝ። አንድ ተጫዋች ያለ ኢንተርሚዲየሪ (ወኪል) ዝውውር ማድረግ አይችልም?
የፊፋ ህግ ላይ ምንም አስገዳጅ ነገር የለም። ሁለት አይነት ወኪልነት ነው ያለው። የተጫዋች እና የክለብ። እየተነሳ ያለው ተጫዋቾችን የተመለከተ ስለሆነ በሱ ላይ ያለውን ነገር በአፅንኦት ልናገር። ፊፋ ምንም አስገዳጅ ህግ አላስቀመጠም። አንድ ተጫዋች ኢንተርሚዲየሪ (ወኪል) መያዝም አለመያዝም መብቱ ነው። እኛም ግዴታ አናደርግም። ከኤጀንቴ ጋር ነው የምፈራረመው ቢልም ባይልም መዘዋወር ይችላል። ስለዚህ ፊፋ የላከው ደንብ ላይ ምንም አስገዳጅ ነገር እንደሌለ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ደንቡ ላይ የተቀመጠው ዋነኛ ነገር የክፍያ መጠኑ ነው። እንደምታውቁት ክፍያው ከግሮዙ 3% እንደሆነ ይደነግጋል። ብዙ ጊዜም ክፍያ ላይ ጭቅጭቅ ስለሚያጋጥማቸው ለክለቦች ይሄንን አሳውቀናል። ይሄንን ደግሞ ለኢትዮጵያ ፉትቦል ኢንተርሚዲየሪዎች ማኅበር ነግረናል። በዓመቱ መጀመሪያም ክቡር ፕሬዝዳንታችም ቁጭ አድርጎ ጉዳዩን ነግሯቸዋል። ስለዚህ በዚሁ መንገድ ነው እኛ የምንቀጥለው።