በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የዞን የማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጋጣሚዎቹን አውቋል።
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው የአፍሪካ የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ይከወናል። በመጀመሪያው ዓመት ውድድር ላይ የሚሳተፉ ስምንት ክለቦችን የሚለየው የዞን የማጣሪያ ጨዋታዎችም ከቀናት በኋላ መደረግ ይጀምራሉ። የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በኬንያ አስተናጋጅነት በሚደረገው የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ላይ ይሳተፋል።
በውድድሩ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ ዘግይቶም ቢሆን ዝግጅት ደብረ ዘይት ላይ የጀመረው ቡድኑ ሐምሌ 10 በሚጀመረው ውድድር ላይ ከማን ጋር በምድብ ጨዋታ እንደሚፋለም ከደቂቃዎች በፊት አውቋል።
በበይነ-መረብ በወጣው የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ላይም የዘጠኝ የቀጠናው ሀገር ክለቦች መኖራቸው ታውቋል። የኢትዮጵያው ተወካይ ንግድ ባንክም በምድብ ሁለት ከደቡብ ሱዳኑ ዪይ ጆይንት ስታርስ እና ከዛንዚባሩ ኒው ጄኔሬሽን ጋር ተደልድሏል።
በወጣው መርሐ-ግብር መሠረት የአሠልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን ሐምሌ 10/11 ከ ዪይ ጆይንት ስታርስ (ደቡብ ሱዳን) እንዲሁም ሐምሌ 12/13 ከ ኒው ጄኔሬሽን (ዛንዚባር) ጋር የምድብ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።