በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድርን አስመልክቶ በፌዴሬሽኑ ስር የሚገኘው የሴካፋ ውድድር አዘጋጅ ብሔራዊ ኮሚቴ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ አበበ ገላጋይ እና የፌዴሬሽኑ ም/ዋና ፀሐፊ እና የኮሚቴው ፀኃፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ በሰጡት መግለጫ ላይ የዝግጀቱ ሁኔታ ማብራርያ የተሰጠበት ሲሆን ከአማራ ክልል ጋር በመቀናጀት የፀጥታ፣ የሆቴል፣፣ የኮቪድ ፕሮቶኮል፣ የሜዳ እና ሎጂስቲክ አቅርቦት እንዲሟላ ጥረት እንደተደረገ ተገልጿል። በአዲስ አበባ እና በባህር ዳር የአዘጋጅ ኮሚቴ በማቋቋም የዝግጅት ሥራው የተሳካ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑም ተብራርቷል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አበበ እንደሚካፈሉ ሲጠበቁ ከነበሩ 13 ሀገራት መካከል ተጋባዧ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ሱዳን የማይሳተፉ ሀገራት መሆናቸውና ሌሎቹ አስራ አንድ አባል ሀገራት ግን የተሳትፎ ማረጋጠጫ እንደሰጡ ጠቁመው ውድድሩ ሲቃረብ ቡድኖቹ ወደ ሀገራችን መግባት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
ከአቶ አበበ አጭር ገለፃ በኋላ ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ሰብሳቢው ማብራርያ ሰጥተዋል።
ኮሮናን በተመለከተ የኮቪድ ፕሮቶኮል እንደሚጠበቅ የገለፁ ሲሆን የባህር ዳር ስታዲየም ከመቶ ሺህ ሰወሰ በላይ መያዝ እንደሚችል የሚገመት በመሆኑ የመጠኑን 1/4ኛ የተመልካች ቁጥር (እስከ 25 ሺህ) ለማስገባት ከሚመለከተው አካል ፍቃድ ጠይቀው በሒደት ላይ እንደሆነ ገልፀዋል።
ከተመልካች ወደ ሜዳ መመለስ ጉዳይ በተጨማሲ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ላይ አቶ አበበ በሰጧቸው ምላሾች በቂ የመለማመጃ ሜዳ መዘጋጀቱን፣ ከዋናው የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተጨማሪ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና የአጼ ቴዎድሮስ ስታዲየሞች ለአማራጭነት ዝግጁ መሆናቸውን፣ ከመንግሥት ድጋፍ በተጨማሪ ስፖንሰሮችን ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን እና ቃል የገቡ እንዳሉ፣ የውድድሩ የምስል ባለ መብት አዛም ቲቪ ጋር በመነጋገር በአማራ ቲቪ ጨዋታዎች እንዲታዩ መታሰቡን፣ ሚዲያዎች እንዲዘግቡ ሁኔታዎች እንደተመቻቹ ገልፀዋል።