አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ አዲስ ክለብ ለማግኘት ከጫፍ ደርሰዋል

በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከሰበታ ከተማ ጋር ያሳለፉት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የጣና ሞገዶቹን ለማሰልጠን ተስማምተዋል።

በፋሲል ከነማ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ሰበታ ከተማን እያሰለጠኑ የነበሩት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ለአንድ ዓመት የፈረሙት ኮንትራት ከቀናት በኋላ ይጠናቀቃል። የአሠልጣኙ ኮንትራት መጠናቀቂያ መባቻ ላይ መገኘቱን ተከትሎ በርካታ ክለቦች አሠልጣኙን ለማግኘት ፍላጎት ቢያሳዩም ጠንካራ ፍላጎት ያሳየው ክለብ ባህር ዳር ከተማ መሆኑ ተሰምቷል።

ከሳምንታት በፊት ከአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር የተለያየው ባህር ዳር ሁለት አሠልጣኞችን በእቅዱ መሠረት በመያዝ ወደ ስብስቡ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ ከርሟል። ክለቡም ከታሰቡት አሠልጣኞች መካከል ቀዳሚው ከሆኑት አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጋር መደበኛ በሆነ እና ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ንግግሮችን ሲያደርግ ቆይቶ ስምምነት ላይ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። 

ከአብርሃም ጋር በሰበታ ከተማ በምክትል አሠልጣኝነት የሰራው ይታገሱ እንዳለ ዋና አሠልጣኙን (አብርሃምን) ተከትሎ ወደ ጣና ሞገዶቹ እንደሚያመራም ተረድተናል። ምናልባት በቅርብ ጊዜ በአዲስ አበባ በሚሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ዋና እና ረዳት አሠልጣኞቹ የሁለት ዓመት ውላቸውን እንደሚፈራረሙ አረጋግጠናል።