የአሠልጣኞች አስተያየት | ሀምበሪቾ ዱራሜ 1-3 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

የማሟያ ውድድሩ የመጨረሻ መርሐ-ግብር ከሆነው ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ አሠልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።

ኤልመዲን መሐመድ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ (ምክትል አሠልጣኝ)

ሦስት ነጥብ እንዲየቀገኙ የረዳቸውም ሦስት ግቦችን በሁለተኛው አጋማሽ ስለማግኘታቸው…?

ጨዋታው እንደ አጠቃላይ ጥሩ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውን ብንቆጣጠርም ትንሽ ከአጨራረስ ጋር የተያያዘ ክፍተት ነበረብን። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ባደረግናቸው የተጫዋች ለውጦች ውጤታማ ነበሩ። ሳሙኤል እና ፀጋ ከገቡ በኋላ ቡድኑ አሸናፊ የሆነበትን ጎሎች አስቆጥሯል። ጨዋታውንም ተቆጣጥረን ወጥተናል።

በውድድሩ ወጥ ብቃት ስላለማሳየታቸው?

ልክ ነው። ዝዋይ ላይ በነበረው ውድድር ላይ ቡድናችን በሂደት እያደገ ነበር የመጣው። ይሄኛው ውድድር ግን ተጫዋቾቻችንን ከበተንን ከ1 ወር ከ15 ቀን በኋላ የመጣ ውድድር ነው። በዚህም ለአጭር ጊዜ ነበር የተዘጋጀነው። ከዚህም መነሻነት የዝግጅት ጊዜው ማጠሩ በምንፈልገው ደረጃ ቡድናችንን እንዳናገኝ ሆነናል። በከፍተኛ ሊጉ ውድድር ላይም ዝግጅቱ አጭር ቢሆንም ከጨዋታ ጨዋታ ለመሻሻል ጊዜ ነበረን። አሁን ግን ውድድሩ አጭር ነው። የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ግን ሊጉ ካለቀ ከ10 ቀን በኋላ ነው ተጫዋቾቻቸውን የጠሩት። ይህ ከውድድር ወደ ውድድር መምጣታቸው ደግሞ ጠቅሟቸዋል።

ከውድድሩ ምን ተማራችሁ? ምንስ የቤት ሥራ ወሰዳችሁ?

በውድድሩ በፕሪምየር ሊጉ የነበሩት ክለቦች ናቸው ያለፉት። እኛ ግን በውድድሩ በደንብ አቅማችንን አይተንበታል። በፕሪምየር ሊጉ ላይም ብንወዳደር ምን ይዘን እንደምንሄድ አሳይተናል። በእንቅስቃሴ ከአዳማም ሆነ ከጅማ ተሽለን ነበር። ወልቂጤ ብቻ ነበር ብልጫ የወሰደብን። የሆነው ሆኖ ይህ ውድድር ለሚቀጥሉት ዓመታት ውድድሮች ጥሩ ግብአት ሰጥቶናል። ሊጉ ላይ ያሉትን ክለቦች በዚሁ ስብስብ መገዳደር ከቻልን መጠነኛ መሻሻል ካደረግን የተሻለ ተፎካካሪ እንደምንሆን አይተንበታል።

ግርማ ታደሠ – ሀምበሪቾ ዱራሜ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጥሩ ለመንቀሳቀስ ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። ባለፈው ጨዋታ የነበረውንም ነገር ለማስቀጠል ሀሳብ ነበረን። ግን ዛሬ የነበረው ፍላጎት ትንሽ አነስተኛ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎችም አለመጠቀማችን እያወረደን ነው የመጣው። በአጠቃላይ በዛሬው ጨዋታ ያሳየነው ብቃት በቂ አይደለም።

በመጀመሪያወረ አጋማሽ እና በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበራቸው እንቅስቃሴ?

እንዳልኩት በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረን ነገር ጥሩ ነበር። ግን በሁለተኛው ግማሽ የመውረድ ነገር አሳየን። የአጨዋወት ቅርፃችንንም ለውጠን ነበር። ነገርግን የተሻለ ነገር ማየት አልቻልንም። በአጠቃላይ ግን ከዝግጅት አንፃር ክፍተት እንዳለብን የሚያሳይ ነገር አለ። በዚህ ላይ ደግሞ ጎሎች ገቡብን።

በውድድሩ ምን አገኛችሁ?

ከዚህ ውድድር ብዙ ነገር ተምረናል። ከአጨዋወት ጋር እና ከተጫዋቾች ባህሪ ጋር የተያያዘ ትምህርት ወስደናል። በተለይ ከፕሪሚየር ሊግ ከመጡት ክለቦች ጋር ያለን የስነ-ልቦና ዝግጁነት በጣም አነስተኛ ነው። ተጫዋቾቹም ከፕሪምየር ሊግ እንደመጡ ስለሚያስቡ ልዩነቱ ተፈጠረ። በአጠቃላይ ዝግጅታችም አነስተኛ ነው። የምንሰራቸው ጥቃቅን ስህተቶች ወደ ጎል ሲቀየርብን ነበር። ይህ ደግሞ ውጤት አሳጥቶናል። ቀጣይ ላለን ውድድርም በቂ ነገር አግኝተናል ብዬ አስባለሁ። ያገኘነውን ዕድል በተለያዩ ምክንያቶች አልተጠቀምንበትም። የሁላችንም ክፍተቶች ቢኖሩበትም በውድድሩ ብዙ ነገር ተምረናል።