ከበርካታ ተጫዋቾች ዝውውር ጋር ስሙ እየተያያዘ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአማካይ መስመር ተጫዋች ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።
በዘንድሮ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከዋንጫ ባለቤቱ ፋሲል ከነማ በ14 ነጥቦች ርቆ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣይ ዓመት ራሱን አጠናክሮ ለመምጣት የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል። እርግጥ ክለቡ የዋና አሠልጣኙን ጉዳይ እስካሁን በግልፅ ባያሳውቅም አሁን ላይ ትኩረቱን የተጫዋቾች ዝውውር ላይ በማድረግ አዳዲስ ተጫዋቾችን የግሉ ለማድረግ እየጣረ ነው።
ድርድሩ ተጠናቆ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማገልገል የፈረመው የመጀመሪያው ተጫዋችም ጋቶች ፓኖም መሆኑ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ያመላክታል። በሌላኛው የመዲናዋ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ መጫወት የቻለው ጋቶች በተጠናቀቀው ግማሽ የውድድር ዓመት በወላይታ ድቻ ጥሩ ጊዜ ማሳለፉ አይዘነጋም።
ከቡና እና ዲቻ በተጨማሪ ለስድስት ወራት በመቐለ 70 እንደርታ ተጫውቶ ያሳለፈው ተጫዋቹ ከሀገር ወጥቶም በሩሲያው ክለብ አንዚ ማካቻካላ፣ በግብፆቹ ኤል ጎውና እና ሀራስ ኤል ሁዳድ እንዲሁም በሳውዲ አረቢያ ዲቪዥን ሁለት ክለብ ለነበረው አል-አንዋር ግልጋሎት ሰጥቷል። ከ2014 ጀምሮ ደግሞ ተጫዋቹ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በፈረሰኞቹ መለያ የእግርኳስ ህይወቱን ለመቀጠል መስማማቱንም ወኪሉ አረጋግጧል።