የፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾች ከዝውውር በፊት የሚያደርጉት የጤና ምርመራ ይዘት ምን ይመስላል?

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ትናንት በተከፈተው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ላይ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር የገለፀውን የተጫዋቾች የጤና ምርመራ ዝርዝር ጉዳዮች የፌዴሬሽኑ የህክምና ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል የሺዋስ ለሶከር ኢትዮጵያ አብራርተዋል።

በአቶ ኢሳይያስ ጂራ የሚመራው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሀገሪቱን እግርኳስ ለማሳደግ ያለሙ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ቀናት በተሰማ መረጃ ደግሞ ትናንት በተከፈተው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ላይ ክለቦች የሚያስፈርሙትን ተጫዋች የጤና ምርመራ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚገልፅ ነው። በአስገዳጅ ሁኔታ ከዘንድሮ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን የተገለፀው የተጫዋቾች የጤና ምርመራን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የህክምና ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል የሺዋስ ጋር ቆይታ አድርገን ተከታዮቹን ምላሾች አግኝተናል።

ይህ የተጫዋቾች የቅድመ ዝውውር የጤና ምርመራ በፕሪምየር ሊግ በሚጫወቱ ተጫዋቾች ላይ ብቻ ለምን ተግባራዊ ይሆናል? በሌሎቹ የሊግ እርከኖችስ ለምን አይደረግም?

ከዘንድሮ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን የምናደርገው የቅድመ ዝውውር የጤና ምርመራ (Pre transfer medical assessment) ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚተገበር ነው። አሁን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ተፈፃሚ የሚሆን ነው። ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ግን በሴቶቹም ሆነ በወንዶቹ ሌሎች የሊግ እርከኖች ላይ ተፈፃሚ እንዲሆን እናደርጋለን። ዋና ጥቅሙ ተጫዋቾች መጫወት በሚያስችላቸው የጤንነት አቋም ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው። ይሄ ሦስት ወገኖችን ይጠቅማል። አንደኛው ራሳቸው ተጫዋቾችን ነው። ሁለተኛው ደግሞ ክለቦችን ነው የሚጠቅመው። ሌላው ተጠቃሚ ወገን ራሱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው።

ተጫዋቾች የምን ምርመራ ነው የሚያደርጉት?

ይህ አሰራር የተዘጋጀው በፊፋ እና ካፍ ቅድመ ውድድር እና ቅድመ ዝውውር ህክምና ይዘት መሠረት ነው። በውስጡ የተጫዋቾች የህክምና ምርመራ ታሪክ ይቀመጣል። ከበፊቱ የህመም እና የጉዳት ታሪክ በተጨማሪ ወቅታዊ ሁኔታቸውም ይካተትበታል። የተሟላ አካላዊ ምርመራ ይኖረዋል። በተለይ ደግሞ ከልብ እንዲሁም ከጡንቻ እና ከአጥንት ጋር የተገናኙ ምርመራዎች ይኖራል። ከዚህ በተጨማሪ የደም የላብራቶሪ ምርመራም ማድረግ ያስፈልጋል።

የምርመራው ዋና ዓላማ ምንድን ነው?

የእኛ ዋናው ዓላማችን በእግርኳስ ሜዳዎች ላይ የልብ ህመምን ምክንያት ያደረገ አደጋ እንዳይከሰት ነው። በተለይ ይህ አደጋ በውጪው ዓለም በተደጋጋሚ ሲከሰት እያየን ነው። ይህ በውጪ ያየነው አደጋ እኛ ጋርም እንዳይደገም እንፈልጋለን። ስለዚህ ትልቁ አጀንዳችን ይህ ነው። ቅድም እንዳልኩት በዚህ አሠራር ክለቦች ተጠቃሚ ናቸው። በሚደረገው የጡንቻ እና የአጥንት ምርመራ የሚያስፈርሙት ተጫዋች ያለበትን ጉዳት ማወቅ ይችላሉ። የማይገለገሉበትን ተጫዋች በከፍተኛ ገንዘብ አስፈርመው ኪሳራ ላይ ከሚወድቁ ቀድመው ተጫዋቹ ያለበትን የጤና ሁኔታ ቢያዩ መልካም ነው።

ስለዚህ ጉዳት ላይ ያለ ተጫዋችን የትኛውም ክለብ ማስፈረም አይችልም ማለት ነው?

የትኛውም ክለብ የተጎዳን ተጫዋች ማስፈረም አይችልም አንልም። የትኛውም ክለብ ዛሬ የተጎዳው ተጫዋች ነገ ተሽሎት ያገለግለኛል ብሎ ካመነ ሊያስፈርመው ይችላል። ግን እኛ በአፅንኦት የምናየው ተጫዋቹ መጫወት ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን ነው። በሚደረጉት ምርመራዎች የማያጫውት ነገር ካለ ተጫዋቹ እንዲጫወት አንፈቅድም። ስለዚህ ጉዳቱ የሚያጫውተው ከሆነ በክለቦቹ ፍቃድ ተጫዋቹ ዝውውሩን እንዲፈፅም ይሆናል።

ቅድም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዚህ ምርመራ ይጠቀማል ብለውኛል። በምን መልኩ እና እንዴት ነው ፌዴሬሽኑ የሚጠቀመው?

ፌዴሬሽኑ የሚጠቀምበት ነገር ከብሔራዊ ቡድን ጋር በተያያዘ ምርመራዎቹ የተደራጀ የመረጃ ቋት እንዲዘጋጅ በመርዳታቸው ነው። ከዚህ በፊት የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ያላቸው የጉዳት ታሪክ የሚቀመጥበት አሠራር የለንም ነበር። ከዚህ በኋላ ግን የምርመራ ውጤቶቹን እያስገባን ወደ ብሔራዊ ቡድን የሚመጡ ተጫዋቾች የጉዳት እና የህመም ታሪክ እንዲቀመጥ እናደርጋለን። ይህን በማድረጋችን ደግሞ የተጫዋቾች የጉዳት ታሪክን ያማከለ የልምምድ አሠጣጥ እንዲሰጥ ይሆናል። እንዲሁም ተጫዋቾቹን እንድንከታተላቸው ያደርገናል።

ከዚሁ ጋር አያይዤ ማንሳት የምፈልገው ፌዴሬሽናችን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ቁጥጥር ጋር በደንብ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ነው። እንደምታውቁት ተቋሙ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ነው በደንብ የሚሰራው። ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ግን በእግርኳሱ ይህንን አምጥተን ተግባራዊ ለማድረግ እንሞክራለን። አንዳንድ ተጫዋቾች በተለያየ ምክንያት የሚወስዱት መድኃኒት ምናልባት በዶፒንግ የሚያስቀጣቸው ይሆናል። ምናልባት ለህይወታቸው እና ለጤናቸው አስፈላጊ የሆነ መድኃኒት ከሆነ ግን በተለየ መልኩ በተዘጋጀው ሌላ ዶክመንት ጉዳዩ ተጣርቶ እንዲወስዱት ይደረጋል።

አንድ ተጫዋች ሊፈርም ሲመጣ ምርመራውን በግሉ ነው የሚያደርገው ወይስ የሚያስፈርመው ክለብ ነው የሚያስመረምረው?

ክለቡ ነው ኃላፊነት ያለበት። የተዘጋጀውን ቅፅ ወይም ፎርም እኛ ጋር (ፌዴሬሽን) መጥተው ይወስዳሉ። ከዛ ከላይ የተገለፁትን የምርመራ አይነቶች ተጫዋቻቸውን የህክምና ቦታ በመውሰድ ያደርጋሉ። ከዛ ውጤቶቹን አስሞልተው ተቀባይነት ያለው ሕጋዊ ማኅተም አስመትተው ነው እኛ ጋር የሚመጡት። ይህ ካልሆነ የትኛውም ዝውውር በፌዴሬሽኑ ፊት ተቀባይነት የለውም። (አይፀድቅም)

ከዘንድሮ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልፀውልኛል። ክለቦቹ ጉዳዩን ተረድተው ተቀብለውታል?

ጥቅሙ የእነሱም ነው። እኛ ከቀናት በፊት ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ደብዳቤ ልከናል። ማኅበሩም ለክለቦቹ እንዲያሳውቅ እና ደብዳቤውን እንዲያሰራጭ አድርገናል። ስለዚህ ያውቁታል ማለት ነው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የፕሪምየር ሊጉ ሥራ አስኪያጆች ለስልጠና (ለክለብ ላይሰንሲንግ) ትናንት ፌዴሬሽን ነበሩ። በተሰጠው ስልጠና ላይም ጉዳዩ ተነስቶላቸው ተነግሯቸዋል። ከትናንት በስትያ የተጠናቀቀው ዝውውርን እና የተጫዋች ምዝገባን የተመለከተው ስልጠና ላይም እንዲያስታውሱት ተደርጓል። ከማወቅ አልፈውም መተው ቅፅ እየወሰዱ ያሉ አሉ።

ቅፁ ክፍያ አለው?

ክፍያ አይባልም። ቅፁ 15 ገፅ ነው። ስለዚህ ክለቦቹ ከእኛ ይህንን ፎርም ሲወስዱ የፕሪንት ገንዘብ ብቻ 150 ብር ይከፍላሉ። ክፍያው ሳይሆን ቁምነገሩ በምርመራው የሚያተርፏቸው በገንዘብ የሚለኩ እና የማይለኩ ኪሳራዎች ናቸው። እኛም በክለብ ለማትረፍ ሀሳብ የለንም። ዋናው በዚህ ሲስተም እንዲገቡ ነው የምንፈልገው።

በመጨረሻ ክለቦቹ የት ነው ምርመራውን የሚያደርጉት? እናንተ በምትጠቁሟቸው ወይስ በፈለጉበት የህክምና ተቋማት?

ክለቦቹ የተገለፁትን ምርመራዎች ማድረግ በሚችል እና በጤና ሚኒስቴር እውቅና ባለው የትኛውም የህክምና ተቋም ማድረግ ይችላሉ። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ቡና ከሌሎቹ ክለቦች በተሻለ ከዝውውር ፊት ይህንን ምርመራ የማድረግ ልምድ አለው። ቡናም በመረጠው የህክምና ቦታ ነው ተጫዋቾቹን አስመርምሮ ዝውውር ሲፈፅም የነበረው። አሁንም እኛ እዚህ አስመርምሩ አንልም። እንዳነሳሁት ግን የተገለፁትን ምርመራዎች ማድረግ በሚችል እና በጤና ሚኒስቴር እውቅና ባለው ተቋም ማስመርመር ይችላሉ። ቅፁን (ፎርሙን) አስሞልተው ከመጡ በኋላ እኛ ትክክለኛ መረጃ መሆኑን እናጣራለን። ከዛ ሁሉ ነገር በትክክለኛው መንገድ ከሄደ ዝውውሩ ይፀድቃል ማለት ነው።

ያጋሩ