የትግራይ ክልል ክለቦችን ለመተካት የሚደረገው የማሟያ የመጨረሻ ጨዋታ በተመሳሳይ ሰዓት ከተደረጉ እና በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ በተከወነ መርሐግብር ወልቂጤ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮን 3-0 በመርታት አዳማን ተከትሎ ማለፉን አረጋግጧል፡፡
በጅማ አባ ጅፋር ተረተው ወደ ዛሬው ጨዋታ የመጡት ኮልፌ ቀራኒዮዎች በአንድ ተጫዋች ላይ ብቻ ለውጥ አድርገዋል፡፡ በቅያሬውም ሀቢብ ከሚል ወጥቶ ክንዱ ባየልኝ ተተክቷል። በአንፃሩ ወልቂጤዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ድል ከተቀናጀው ስብስባቸው ውስጥ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር ም/ል ኮሚሽነር ዱቤ ጅሎ የኢትዮጵያ እግር እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ጨዋታውን አስጀምረውታል፡፡ በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት የጀመረው የኮልፌ እና ወልቂጤ ወሳኝ ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ጥድፊያ መሰል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ከመመልከት በዘለለ ሁለቱም ቡድኖች የመጠባበቅ ዓይነት መልክ የነበረው የጨዋታ ሂደት ሲከተሉ በደንብ ማስተዋል ችለናል፡፡ ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር ሁለቱም ቡድኖች ኳስን በመቆጣጠሩ ረገድ የተዋጣላቸው ቢሆንም ከግብ ጋር ለመገናኘት የሚፈጥሩት ጥረት እምብዛተደምድሟል፡፡
ጨዋታው ተጋምሶ 29ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያ የግብ አጋጣሚን ተመልክተናል፡፡ የኮልፌው የመስመር ተከላካይ አቡበከር ካሚል ከግራ በኩል መሬት ለመሬት ወደ ወልቂጤ የግብ ክልል ሲልክ ብቻውን ከግቡ ትይዩ የነበረው አንዋር ዱላ በቀላሉ ወደ ጎልነት ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ ጀማል ጣሰው በሚገርም ብቃት አድኖበታል፡፡ ከዚህች ሙከራ በኋላ ከነበረው የውሀ ዕረፍት መልስ ወልቂጤ ከተማዎች በሁለቱም የመስመር ኮሪደር በኩል በተደጋጋሚ በኮልፌ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ጥረት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ በዚህም ተሳክቶላቸው 31ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል፡፡በቀኝ የኮልፌ የግብ ክልል አካባቢ ተከላካዮች በአቡበከር ሳኒ ላይ በሰሩት ጥፋት የተገኘውን ቅጣት በኃይሉ ተሻገር በረጅሙ ሲያሻማ አቡበከር ሳኒ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ሰራተኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ከጓሏ በኋላ ሁለት ደቂቃዎች እንደተቆጠሩ አሜ መሀመድ ከሳጥን ጠርዝ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ኃይማኖት አድኖበታል፡፡ አጋማሹም በወልቂጤ መሪነት ተደምድሟል፡፡
ከዕረፍት መልስ ይበልጥ ተነቃቅተው ወደ ሜዳ የተመለሱት ወልቂጤ ከተማዎች እንዳሳዩት ፈጣን የሽግግር እንቅስቃሴ ሁሉ ጎል ለማስቆጠር የፈጀባቸው ደቂቃ ስምንት ነበር፡፡ እጅግ በሚማርክ ቅብብል አሜ ፣ አቡበከር እና አብዱልከሪም በኮልፌ የግብ ክልል ከደረሱ አህመድ ሁሴን ጋር ኳሷ ደርሳ በቄንጠኛ አኳኋን አቀብሎት አብዱልከሪም ወርቁ ሰጥቶት አማካዩም በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፎ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስመዝቧል፡፡ እንደ አጀማመራቸው መዝለቅ ያልቻሉት ኮልፌዎች በዚህ የጨዋታ አጋማሽ ለማንሰራራት የሚያደርጉት ጥረት ደካማ በመሆኑ በወልቂጤ ብልጫ ሊወሰድባቸው ግድ ብሏል፡፡
ኳስን በመቆጣጠር አብዱልከሪም ወርቁ እና በኃይሉ ተሻገርን ማዕከል ባደረገ እንቅስቃሴ በመስመር ኳስን በመጣል የተጫወቱት ወልቂጤ ከተማዎች ሦስተኛ ግባቸውን አግኝተዋል፡፡አሁንም በጥሩ የጨዋታ ሂደት የመጣችን አጋጣሚ አሜ መሀመድ ጋር ደርሳ ተጫዋቹ በቀጥታ ወደ ሳጥን ሲልካት አህመድ ሁሴን አግኝቶ ወደ ጎልነት በመለወጥ የቡድኑ የግብ መጠን ወደ ሦስት አሳድጓል፡፡ በጨዋታው እጅጉን ቀዝቀዝ ባለ አካሄድ ሲጓዙ የነበሩት ኮልፌ ቀራኒዮዎች 67ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሰዒድ ኑሩ መትቶት ጀማል ጣሰው ያዳነበት እና ብሩክ ሙሉጌታ በጭማሪ ደቂቃ ሞክሮ ጀማል አሁንም የመለሰባቸው ቡድኑ ያደረጋቸው ሁለት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ነበሩ። በቀሩት ደቂቃዎች ጨዋታው ተጨማሪ ግቦችን ሳንመለከት በወልቂጤ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡በዚህም ወልቂጤ ሁለተኛው መመለሱን ያረጋገጠ ቡድን ሆኗል፡፡