ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር በአዳማ ቢረታም የማሟያ ውድድሩ አላፊ ቡድን መሆኑ ተረጋግጧል

አንደኛውን የማሟያ ውድድሩ አላፊ ክለብ ለመለየት የተደረገው የአዳማ እና የጅማ ጨዋታ በአዳማ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኮልፌ ቀራኒዮን ረትቶ ለዛሬው ወሳኝ ጨዋታ የተዘጋጀው ጅማ አባጅፋር ድል ከተቀዳጀበት ጨዋታ አንድ ለውጥ ብቻ አድርጓል። በዚህም ዋውንጎ ፕሪንስ ወጥቶ ሱራፌል ዐወል ወደ ሜዳ ገብቷል። አዳማ ከተማ በበኩሉ ቀዳሚ አላፊ ቡድን መሆኑን ካረጋገጠበግ ጨዋታ ሦስት ለውጦችን አድርጓል። በዚህም ሠይፈ ዛኪር፣ አሚኑ ነስሩ እና ሚሊዮን ሠለሞን ወጥተው ላሚን ኩማሬ፣ እዮብ ማቲዮስ እና ታፈሰ ሠርካ በቋሚነት ጨዋታውን ጀምረዋል።

የዕለቱን የክብር እንግዶች ሠላምታ በመስጠት የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንደ አየር ፀባዩ ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር በማሳየት መከናወን ይዟል። የሁለቱም ቡድን ተጫዋቾችም ቶሎ ቶሎ ኳስ በመነጣጠቅ ያልተረጋጋ አጨዋወት ሲከተሉ ተመልክተናል። ጨዋታው ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን አዳማ ከተማ የመጀመሪያ ሙከራውን ጅማ ላይ ሰንዝሯል። በዚህም አብዲሳ ጀማል ለበቃሉ ገነነ ጥሩ ኳስ አመቻችቶለት የነበረ ቢሆንም በቃሉ የሞከረውን ኳስ የግብ ዘቡ አቡበከር ኑሪ አውጥቶታል።

ቀስ በቀስ በጨዋታው ያላቸውን ተፅዕኖ ለማምጣት መጣር የጀመሩት ጅማዎች በበኩላቸው በ14ኛው ደቂቃ የራሳቸውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ቡድኑ በቀኝ መስመር በኩል ወደ አዳማ የግብ ክልል አምርቶ በዋለልኝ ገብሬ አማካኝነት ጥቃት ፈፅመዋል። በድጋሜ በ23ኛው ደቂቃ የአዳማን አማካዮች የኳስ ስህተት ለመጠቀም የጣሩት ጅማዎች ተመስገን ደረሰ ለንጋቱ ገብረስላሴ አቀብሎት ንጋቱ ሳይጠቀምበት በቀረው ኳስ አስቆጪ ዕድል አምክኗል። ቡድኑ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የቅጣት ምት አግኝቶ በመላኩ ወልዴ አማካኝነት ወደ ግብ ቢልከውም ቀዳሚ መሆን ሳይችል ቀርቷል።

ረጃጅም ኳሶች የበዙበት ጨዋታ ላይ አዳማ ከተማ በ39ኛው ደቂቃ በጥሩ የኳስ ፍሰት ወደ ጎል ደርሶ ሙከራ አድርጎበት ነበር። በዚህም አብዲሳ ጀማል ከኤልያስ ማሞ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥርም ግብ ጠባቂው አቡበከር አድኖበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታም ያለ ግብ ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

የሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የስፖርት ኮሚሽም ኮሚሽነር አቶ ኤልያስ ሽኩር እና ምክትል ኮሚሽነር የሆኑ አቶ ዱቤ ጅሎ ጨዋታውን ለመታደም ስታዲየም መጥተዋል። ይሄኛውም አጋማሽ እንደ መጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር ቢያሳይም በ58ኛው ደቂቃ ላይ ግን እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አስተናግዷል። በዚህ ደቂቃም በመስመሮች መካከል ራሱን ነፃ አድርጎ ኳስ ያገኘው አብዲሳ ጀማል ወደ ጎል አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ለመሆን የከለከለው የግቡ ቋሚ ነበር።

ከላይ የተጠቀሰው ሙከራ ከተደረገ ከአስር ደቂቃዎች በኋላም አዳማ ሌላ አስደንጋጭ ሙከራ አድርጓል። በዚህም ኤልያስ ማሞን ቀይሮ የገባው ማማዱ ኩሊባሊ ጀሚል ያቆብ ጥሩ የመስመር ላይ ሩጫ አድርጎ ያሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥርም አቡበከር ኑሪ በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶታል። ከደቂቃ በኋላም ቡድኑ ዳግም የጅማ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ገብቶ የጠራ የግብ ሙከራ ቢያደርግም የግብ ዘቡ አቡበከር አሁንም ኳሱን አምክኖታል።

እጅግ ተሻሽለው ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት አዳማዎች አሁንም ጅማ ላይ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል። በ70ኛው ደቂቃም በአጥቂያቸው አብዲሳ አማካኝነት ወደ ተጋጣሚ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ተጉዘው ግብ ለማስቆጠር ቢዳዱም ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ሲያድን የነበረው ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ ያልተገባ አጨዋወት ተጫውቶ ግብ ሳይቆጠር ቀርቷል። ግብ ጠባቂው ከግብ ክልሉ ውጪ በሰራው ጥፋትም በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲሰናበት ሆኗል። የተሰራው ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምትም ጀሚል ያቆብ መጥቶት የነበረ ቢሆንም ከሰከንዶች በፊት ተቀይሮ የገባው በረከት አውጥቶታል።

የቁጥር ብልጫ ተወስዶባቸው ይባስ ጨዋታውን መቆጣጠር ያልቻሉት ጅማዎች በ82ኛው ደቂቃ ግብ አስተናግደዋል። በዚህ ደቂቃም ማማዱ ኩሊባሊ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት የደረሰውን እጅግ ጥሩ ኳስ እርጋታ በተሞላበት መንገድ ወደ ጎልነት ቀይሮት አዳማ መሪ ሆኗል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ የግብ ማግባት ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታ በአዳመቀ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ቀድሞ ማለፉን ያረጋገጠው አዳማ ከተማ ነጥቡን 13 በማድረስ የማሟያ ውድድሩን ደረጃ ሠንጠረዥ አናት ይዞ አጠናቋል። ጅማ አባጅፋርም በጨዋታው ሦስት ነጥብ ቢያስረክብም በሌላ ጨዋታ የኮልፌ መሸነፍ ጠቅሞት በሰባት ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አላፊ ሆኗል።

ያጋሩ