የማሟያ ውድድሩ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዳሰሳ

የማሟያ ውድድሩ ሁለት አላፊ ቡድኖችን የሚለዩትን ሁለት ወሳኝ ጨዋታዎች እና አንድ ዓላማ ቢሱን መርሐ-ግብር እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።

👉ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ ከ ወልቂጤ ከተማ (4:00)

አንዱን የማሟያ ውድድር አላፊ ክለብ የሚለየው መርሐ-ግብር እጅግ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቷል። በተለይ ሁለቱም ክለቦች ተቀራራቢ የጨዋታ መንገድ መከተላቸው እና አሸናፊው ክለብ ሁለተኛ አልያም ሦስተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ለሁለት ሳምንት የቆየውን ውድድር ዓላማ ስለሚያሳካ ጨዋታው በትልቅ ጉጉት ይጠበቃል።

በአሠልጣኝ መሐመድኑር የሚመራው ኮልፌ በውድድሩ እጅግ ወጣ ገባ አቋም እና ቀድሞ የማይገመት ውጤት ከሚያስመዘግቡ ክለቦች ግንባር ቀደሙ ነው ቢባል ማጋነን አይደለም። በተለይ በመጀመሪያው የሀምበሪቾ ጨዋታ የሚታወቅበትን የኳስ ጋር እንቅስቃሴ ያስመለከተው ቡድኑ በቀጣዩ የአዳማ ጨዋታ እጅግ ወርዶ ታይቷል። በሦስተኛው ዙር የውድድሩ ጨዋታ ደግሞ የወትሮ ብቃቱን በማግኘት ኤሌክትሪክን ሁለት ለምንም አሸንፎ የማለፍ ተስፋውን ቢያለመልምም ከሦሰት ቀን በፊት በተደረገው የአባጅፋር ጨዋታ ደግሞ ከጥንካሬው ስህተቱ አመዝኖ እጅ ወጥቶ ወጥቷል። ታዲያ ይህ በወጥነት ወጥ ያልሆነው የቡድኑ ብቃት ተሻሽሎ በነገው ወሳኝ ጨዋታ የማይመጣ ከሆነ ቡድኑ ፈተና ላይ ሊወድቅ ይችላል። ምንም ቢሆን ምንም ግን ቡድኑ ከኳስ ጋር ዘለግ ያለውን ጊዜ በማሳለፍ ጨዋታውን እንደሚከውን ይታመናል። ቡድኑ በማሟያ ውድድሩ አላፊ ለመሆን በእጁ ያለውን ጨዋታ ማሸነፍ አልያም አቻ ወጥቶ በአንድ ነጥብ የሚበልጠው አዳማ ከተማ በስምንት ግቦች እንዲሸነፍ መጠበቅ የግድ ይለዋል።

በአሠልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው እጅግ እየተሻሻለ የመጣው ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ ማሸነፍ አልያም አቻ መውጣት ዋና ዓላማውን የሚያሳካለት ይሆናል። ወልቂጤ በኤሌክትሪኩ ጨዋታ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል ሲወስድ ያሳየው የሜዳ ላይ ብቃት የሚገርም ነበር። ከምንም በላይ ተጫዋቾቹ ላይ ሲታይ የነበረው ርሀብ፣ ተጋጣሚ ኳስ ሲነጥቅ መልሶ የማስጣል ሂደት፣ የመከላከል ጥንካሬ እና የጎል ፊት አንበሳነት ሳይደነቅ ማለፍ የለበትም። ይህ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በነገው ጨዋታም የሚደገም ከሆነ ቡድኑ አትራፊ የሚሆን ይመስላል። ይህ ቢሆንም ግን የነገው ተጋጣሚ ኮልፌ ለቡድኑ ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆን ይታሰባል። በተለይ የኮልፌ የአማካይ መስመር ተጫዋቾች አይደክሜነት እና ኳስን ለረጅም ጊዜ በእግራቸው ስር ማቆየት ፈተና ሊሆንበት እንደሚችል ይታሰባል። የሆነው ሆኖ ግን በቁጥር በዝቶ ለማጥቃት ሲሞክር የሚታየው ቡድኑ በፈጣኖቹ የወገብ በላይ ተጫዋቾች ሊጠቀም ይችላል። የተጠቀሰው ምክንያት አሳማኝ ቢሆንም ግን አንድ ነጥብ አላፊ የሚያደርገው ቡድኑ ሦስት ነጥብ ላለማጣት ተከላክሎም ሊጫወት እንደሚችል መታሰብ የግድ ይሏል።

👉ጅማ አባጅፋር ከ አዳማ ከተማ (4:00)

ሌላኛውን የማሟያ ውድድር አላፊ ቡድን የመለየት አቅም ያለው መርሐ-ግብር የጅማ አባጅፋር እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ነው። እርግጥ አዳማ ከተማ የመጀመሪያው አላፊ ቡድን መሆኑ በአራተኛ ዙር ጨዋታዎች ቢረጋገጥም የጅማ አባጅፋር ጉዳይ ግን አለየም። ጅማም ነገ አዳማን የሚያሸንፍ ከሆነ፣ እርሱም ሆነ ኮልፌ የሚሸነፉ ከሆነ ወይም አቻ የሚወጡ ከሆነ (እርሱ እና ኮልፌ) ማለፉን ያረጋግጣል።

ኮልፌን ሁለት ለምንም ረትቶ ለዚህኛው ጨዋታ የሚዘጋጀው ጅማ በጥሩ ሞራል ላይ ያለ ይመስላል። በሜዳም ላይ እንቅስቃሴ ክለቡ አዎንታዊ ነገር እያሳየ ይገኛል። ከምንም በላይ እንደ ቡድን የመጫወት ብቃቱን በማሳደግ በሁለቱም ሳጥኖች (በራሱ እና በተጋጣሚ) ላይ ጠንካራ በመሆን ለተጋጣሚ ቡድን አስቸጋሪ ቡድን እየሆነ እንደመጣ እየታየ ነው። ከዚህም መነሻነት በነገው ጨዋታ ጅማ ይሄንን መሻሻሉን የሚያስቀጥል ከሆነ ለአዳማ ከተማ ከባድ ተፎካካሪ ሊሆን ይችላል። በዋነኝነት ደግሞ ቀጥተኛ አጨዋወትን ተግባራዊ በማድረግ ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂዎቹ በመላክ እና ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚሰነዘር ፈጣን ሽግግር ግብ ለማስቆጠር እንደሚታትር ይጠበቃል።

የማሟያው ውድድር ቀዳሚ አላፊ ቡድን መሆኑን ቀድሞ ያረጋገጠው አዳማ ከተማ ነገ የሚያደርገው ጨዋታ የውድድሩን ደረጃ ሠንጠረዥ አናት ከመያዝ የዘለለ ትርጉም አይሰጠውም። የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ የመሳተፍ ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ ስላልተረጋገጠ ደግሞ ቀዳሚውን ቦታ ይዞ ሂደቱን መጠባበቅ አስፈላጊ ነው። ምንም ይሁን ምንም ግን ቡድኑ ያለ ከፍ ያለ ጭንቀት ጨዋታውን እንደሚቀርብ ይገመታል። ይህ ጭንቀት እና ጫና አልባ አቀራረብ ደግሞ ተጫዋቾች በነፃነት እንዲጫወቱ አዎንታዊ አበርክቶ ቢኖረውም በተቃራኒው የትኩረት ማነስ እና ያለ ዓላማ የመጫወት ችግርን ይዞ ብቅ ሊል ይችላል። ከዚህም መነሻነት የቡድኑ አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የተጫዋቾቻቸውን የጨዋታ ዝግጁነት በተገቢው ደረጃ ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ውጪ ግን የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጠቀሪው እና ዝቅተኛ ግብ አስተናጋጁ ክለብ ነገም በጠንካራነቱ ሊቀጥል ይችላል።

👉ሀምበሪቾ ዱራሜ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (8:00)

ዓላማ ቢስ የሆነው የሀምበሪቾ ዱራሜ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ መርሐ-ግብር ከማሟላት በዘለለ ትርጉም የለውም። ሁለቱም ቡድኖች የማሟያ ውድድሩ ወዳቂ ክለብ መሆናቸውን አረጋግጠው ወደ ሜዳ ስለሚገቡም የወረደ ፉክክር እንደሚታይበት ይታሰባል። የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞችም በውድድሩ የመጫወት ዕድል ያላገኙ ተጫዋቾችን በአብዛኛው አስገብተው እንደሚጫወቱ ይገመታል።

በአራት ጨዋታ አንድም ነጥብ ያላገኘው ሀምበሪቾ በአራተኛ ዙር ጨዋታ በአዳማ ቢሸነፍም በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ያሳየት መሻሻል መልካም ነበር። ሳይደክሙ ሜዳውን አካለው ሲጫወቱ የነበረበትም መንገድ ጥሩ ነበር። ምናልባት ከማለፍ ጫናዎች ነፃ ሆነው የሚያደርጉትን የነገ ጨዋታም በዚሁ የመሻሻል ሂደት ካከናወኑት “ብቸኛ ነጥብ ሳያገኙ የወጡ” የሚለውን ተቀፅላ የሚያጠፉ ይሆናል።

በአሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተና የሚመራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በወልቂጤው ጨዋታ ለግማሽ ደርዘን የተጠጋ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብቶ ያሳየው ብቃት እጅግ ደካማ ነበር። በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይም ክፍተቶች እና አለመናበቦች ሲታዩ አስተውለናል። በተለይ ጨዋታው ግማሽ ሰዓት ሳይሞላ ግብ ካስተናገዱ በኋላ የመረጋጋት ባህሪ ሳይታይባቸው ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ወጥቶ ነበር። ይህ የመናበብ እና እንደ ቡድን የመጫወት ብቃት በነገው ጨዋታ ታርሞ ከመጣ ፋይዳ ባይኖረውም ቡድኑ ነጥቡን ስድስት አድርሶ ውድድሩን ይቋጫል።