በተጋባዥነት በሴካፋ ውድድር ላይ እንደምትሳተፍ ሲጠበቅ የነበረው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምክንያቱ ባልታወቀ ጉዳይ ከውድድሩ ራሷን አግላለች ቢባልም ከሦስት ቀን በኋላ ለውድድሩ ሀገራችን እንደምትገባ ታውቋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ የምታስተናግደው የቀጠናው ውድድር (ሴካፋ) በአስራ አንድ አባል ሀገራት እና አንድ ተጋባዥ ሀገር መካከል እንደሚደረግ ቀድሞ ሲነገር ቆይቷል። ይህ ቢሆንም በተጋባዥነት በውድድሩ ለመሳተፍ ፍላጎት ያሳየችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሱዳን እንደማይሳተፉ ለሴካፋ ማሳወቃቸው ከቀናት በፊት ይፋ ቢሆንም ተጋባዧ ሀገር አሁንም በውድድሩ ላይ እንደምትሳተፍ እየገለፀች ትገኛለች።
በአዲሱ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ዧን-ክሎድ ሎቦኮ የሚመራው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን ከሳምንታት በፊት ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርቦ ዝግጅቱን ሲያደርግ ከርሟል። የዝግጅት ጊዜውን እና በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ውድድር ላይ ያለውን እቅድ በተመለከተ አሠልጣኝ ዧን-ክሎድ ሎቦኮ መግለጫ ሰጥተዋል።
አሠልጣኙ በሰጡት መግለጫም “እቅዳችን ትልቅ ነው። ወጣት ተጫዋቾችንም ለማብቃት እንጥራለን። ከምንም በላይ ተጫዋቾቹ በትልቅ ደረጃ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዲያደርጉ እና ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ነው” ብለዋል። አሠልጣኙ አያይዘውም በሴካፋ ውድድር የሀገራቸውን ባንዲራ በተሻለ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። ለሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች በተሰጠው መግለጫም ብሔራዊ ቡድኑ በኬንሻሳ የሚያደርገውን ዝግጅት አገባዶ ረቡዕ ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዝ ተገልጿል።