“በ2014 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ለማዘጋጀት መልስ የሰጡት ክልሎች ሁለት ብቻ ናቸው “

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የ2014 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን ለማዘጋጀት ለክለቦች መስፈርት የተካተተበት ደብዳቤ የላከ ቢሆንም ቀኑን ጠብቀው ምላሽ የሰጡት ሁለት ክልሎች ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2013 የውድድር ዘመን ካለፉት ዓመታት በእጅጉ በተሻለ አኳሀን ከወር በፊት በፋሲል ከነማ አሸናፊነት መደምደሙ ይታወሳል፡፡ እንደ መጀመሪያ ዓመት ውድድሩ ከሞላ ጎደል በጥሩ ሁኔታ ፍፃሜውን ያገኘ ቢሆንም ከሜዳ እና መሰል ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ግን ጉድለቶች ታይተውበታል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ ዘንድሮ የታዩ ጉድለቶችን ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ለመቅረብ ከወራት በፊት ዘንድሮ በሊጉ ተወዳዳሪ ለነበሩት አስራ ሦስቱም ቡድኖች ውድድሩን እንዲያዘጋጁ መስፈርት የያዘ ደብዳቤ መላኩ ይታወሳል፡፡ 

እስከ ሰኔ 30 – 2013 ድረስ የመጨረሻ ቀነ ገደብ ተቀምጦ ለክለቦች በተላከው ደብዳቤ በዋናነት የመጫወቻ ሜዳ፣ የስታዲየም ሁኔታ፣ የመለማመጃ ሜዳ እና በከተሞች የሚገኙ ሆቴሎች ዘንድሮ ከነበረው ክፍተት አንፃር በምን አይነት መልኩ መዘጋጀት አለበት የሚሉትን የያዘ ነበር። ይሁን እንጂ ለክለቦቹ ከተላከ በኃላ ላሉበት ክልል አሳውቀው መልስ የሰጡት ሁለት ክልሎች ብቻ መሆናቸውን ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ የሊግ ካምፓኒው የውድድር እና ሥነ ስርዓት ሰብሳቢ ገልፀውልናል፡፡

“መስፈርት አውጥተን ለክለቦች ደብዳቤ ልከን ነበር። በተቀመጠው መስፈርት መልስ የሰጡን ግን የአማራ እና የሲዳማ ክልል ብቻ ናቸው። ይሄም ማለት በሀዋሳ እና ባህር ዳር ውድድሩን ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አግኝተናል፡፡ቢሆንም ግን ሙሉ በሙሉ በእኛ ረገድ የተሟላ ብለን የያዝነው የባህርዳርን ስታዲየም ነው። የሀዋሳ ሜዳ ግን እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ነግረናቸዋል፡፡ ክልሎች በፍቃደኝነት ነበረ ለማዘጋጀት መነሳሳት የነበረባቸው። ግን ይሄን ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት እጅግ ያነሰ ነው፡፡ እኛ እየጠየቅን ነው ውድድሩን እንዲያዘጋጁ እያደረግን ያለነው በዚህ መልኩ ግን መቀጠል ስለሌለበት ዲኤስቲቪ ለራሱ ቅድመ ዝግጅት እንዲያመቸው የሚጀመርበትን ቀን እንድናሳውቀው ይፈለጋል። ያ እንዲሆን ደግሞ ሁሉም ክለቦች የወጣውን መስፈርት የሚያሟላ ሜዳ፣ ሆቴል እና ሌሎች የተቀመጡ መመሪያዎችን የሚያሟላ ሜዳ ካላቸው ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የዘንድሮው ውድድራችን በመሀል ጨዋታ እየተካሄድ የጣሊያን ሴሪ አ እና ሌሎች ጨዋታዎች በመሐል ጣልቃ እየገቡ ሲስተጓጎል ነበር፤ ይሄ መሆን የለበትም። ለዚህም ከአሁን እየተዘጋጀን ስለሆነ በተላከው ደብዳቤ መሠረት አሁንም መልስ ክለቦች ሊሰጡ ይገባል።”

እስከ ሰኔ 30 ቀነ ገደብ ተቀምጦ ለክለቦች የተላከው መስፈርት ቀኑ ቢያልፍም ክለቦች እስከዚህ ወር አጋማሽ መልስ እንዲሰጡ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡

ያጋሩ