አሥራት ቱንጆ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ይቀጥላል?

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ጥሩ ብቃት ያሳየው አሥራት ቱንጆ ከቡናማዎቹ ጋር የመቀጠል እና አለመቀጠሉ ጉዳይ እየለየ መጥቷል።

በ2009 ክረምት ጅማ አባ ጅፋርን ለቆ ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው አሥራት ቱንጆ በቡናማው መለያ ራሱን እያጎለበት ለቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ሆኗል። በተለይ ለአሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ አጨዋወት አመቺ የሆነው የመስመር ተከላካዩ ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ስሙ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲያያዝ ሰንብቷል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ግን ተጫዋቹን ለማቆየት ከቀናቶች በፊት ድርድር ቢያደርጉም ውይይቱ ያለ ስምምነት ተጠናቆ ነበር። በዚህም በመጀመሪያው የድርድር ምዕራፍ ተጫዋቹ ከክለቡ ጋር ሳይስማማ በመቅረቱ ከክለቡ እንደሚለቅ ሲነገር ነበር።

ከሦስት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን ተቀላቅሎ የነበረው ተጫዋቹ በዛሬው ዕለት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ባህር ዳር ከማቅናቱ በፊት ከኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንር አቶ ክፍሌ አማረ ጋር በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ድርድር ማድረጋቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በድርድሩም ተጫዋቹ በአብዛኛው ነገሮች መስማማቱ እና ተጫዋቹ ከቡና ጋር የሚቆይበትን መንገድ ሁለቱ አካላት ከስምምነት መድረሳቸውን ሰምተናል። ለብሔራዊ ግዳጅ ማምሻውን ወደ ባህር ዳር ያቀናው ተጫዋቹም በቀጣዮቹ ቀናት ስምምነቱን በወረቀት እንደሚያሰፍር ይጠበቃል።

ያጋሩ