በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በቅርቡ እስራኤል ለተጓዘው የታዳጊ ቡድን ምስጋናን አቀረቡ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከእስራኤል ጋር ባደረገው መልካም ግንኙነት በቅርቡ ወደ ሀገሪቱ ተጉዞ የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ ለተመለሰው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም የኢትዮጵያ እና የእስራኤል ግንኙነት በተመለከተ ዛሬ ከሰዓት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ግብዣን አድርገዋል፡፡

በተጠናቀቀው ወር ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከእስራኤል አቻው ጋር በትምህርት፣ ስልጠና፣ ስፖርት ማኔጅመንት፣ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ያቀፈ ስምምነት የፈፀመ ሲሆን በወቅቱም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን በተመሳሳይ ዕዶሜ ላይ ከሚገኘው የእስራኤል ብሔራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታን አድርጎ መመለሱ ይታወሳል፡፡ ይሄን መልካም የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በኢትዮጵያ የእስራኤል ኢምባሲ በዛሬው ዕለት በፅህፈት ቤቱ የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን አባላት እና የፌድድሬሽኑ ከፍተኛ የስራ አካላት በተገኙበት የምስጋና እና የምሳ ግብዣን አካሂዷል።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ የምስጋናው ዋና አላማ የኢትዮጵያ እና የእስራኤል እግርኳስ ፌዴሬሽኖች የጀመሩት መልካም መቀራረብ ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን አያይዘውም የኢትዮጵያ እና የእስራኤል ዲፕሎማሲዊ ወዳጅነት 30ኛ ዓመቱ ላይ በመድረሱ ሁለቱን ነገሮች በጋራ በማጣመር ለማመስገን በሚል ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡ በመቀጠል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የተጀመረው የትብብር መንፈስ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አውስተው ግንኙነታችን ከእስራኤል ጋር መጀመሩ በሁሉም ረገድ ጥቅሙ የጎላ መሆኑን በመናገር እስራኤል ለጀመረችው የወዳጅነት ግንኙነት በማመስገን እግር ኳሳችንን ለማሳደግ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡

በሥነ ስርዓቱ ላይ የኢምባሲው ሰራተኞች እና የፌዴሬሽኑ የስራ ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የኢትዮጵያ እና የእስራኤልን 30ኛ ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚያሳይ 30 ቁጥር ያለበት መለያ እና የምሳ ግብዣን በመጨረሻ አካሂደው ሥነ ስርዓቱ ተጠናቋል፡፡