የፊታችን ቅዳሜ ለሚጀመረው የሴካፋ ውድድር በአዲስ አበባ ሲዘጋጅ የከረመው ብሔራዊ ቡድኑ አንድ ተጫዋች ቀንሶ በምትኩ ለአንድ ተጫዋች ጥሪ በማድረግ አመሻሽ ባህር ዳር ደርሷል።
ለ41ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ከሰኔ የመጀመሪያ ቀናት አንስቶ ሲዘጋጅ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አመሻሽ ላይ ውድድሩ ወደሚደረግበት ባህር ዳር ከተማ አቅንቷል። እርግጥ ብሔራዊ ቡድኑ ውድድሩ ከመራዘሙ በፊት ወደ ባህር ዳር አቅንቶ የነበረ ቢሆንም የውድድሩ መጀመሪያ የቀናት መገፋት ከታወቀ በኋላ ዳግም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ዝግጅቱን በካፍ የልዕቀት ማዕከል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ማድረግ ቀጥሏል። ልምምዶችን ከማድረጉ በተጨማሪ ከሀገር ውስጥ ክለቦች ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ሲያደርግ የነበረው ቡድኑ የአዲስ አበባ የዝግጅት ምዕራፉን አገባዶ 11 ሰዓት ሲል ባህር ዳር ከተማ ገብቷል። ልዑካን ቡድኑም መቀመጫውን በብሉ ናይል (አቫንቲ) ሆቴል ማድረጉ ታውቋል።
ሶከር ኢትዮጵያ ከምንጮቿ ባገኘችው መረጃ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ስንታየሁ መንግስቱን ከስብስባቸው ቀንሰዋል። አሠልጣኙ ተጫዋቹን የቀነሱት በስብስባቸው ውስጥ በርካታ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ስላላቸው እንደሆነም ተረድተናል። ስንታየሁን ሳይዝ ወደ ባህር ዳር ያቀናው ብሔራዊ ቡድኑ በተከላካይ መስመሩ ላይ ባየው መሳሳት ለወልቂጤ ከተማው የመስመር ተከላካይ ረመዳን የሱፍ ጥሪ አቅርቧል። በትናንትናው ዕለት የክለብ ግዳጁን የጨረሰው ተጫዋቹም በነገው ዕለት ስብስቡን እንደሚቀላቀል ሰምተናል።