ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ የሚደረገው የሴካፋ ውድድር የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ዛሬ ከሰዓት ይከናወናል።
41ኛው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በ23 ዓመት በታች ቡድኖች መካከል ከሐምሌ 10 ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ ይደረጋል። ምንም እንኳን በውድድሩ የሚሳተፉ የቀጠናው ብሔራዊ ቡድኖች ቀስ በቀስ ራሳቸውን እያገለሉ ቢመጡም ባሉት ሀገራት የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብሩ በዛሬው ዕለት በበይነ-መረብ እንደሚከናወን ለማወቅ ችለናል። ትናንት አመሻሽም ሴካፋ ለአባል ሀገራቱ የውድድሩ የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ዛሬ እንደሆነ በላከው መልዕክት አስታውቋል።
ለእርግጠኛ መረጃዎች እምብዛም ክፍት ያልሆነው ሴካፋ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚከናወነው ውድድር የሚሳተፉ ሀገራት 20 ሺ ዶላር መክፈል እንዳለባቸው ማስታወቁ ይታወሳል። ይህንን መረጃ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስም ይህንን ክፍያ የከፈሉት ሀገራት ስድስት መሆናቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን ነግረውናል። ሴካፋ ኦንላይን የተሰኘው ድረ-ገፅ ይዞት በወጣው መረጃ መሠረት ደግሞ ዩጋንዳ፣ ኤርትራ፣ ቡሩንዲ፣ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ በዛሬው የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ላይ እንደሚካተቱ አትቷል።
በተያያዘ ሶማሊያ እና ሩዋንዳ በውድድሩ እንደማይሳተፉ ቀድሞ መገለፁ የሚታወቅ ሲሆን የዛንዚባር እግርኳስ ፌዴሬሽን ደግሞ እስከ ትናንት መሳተፍ እና አለመሳተፋቸውን ባለማሳወቃቸው በእጣ ማውጣቱ ላይ ላይካተቱ እንደሚችሉ ተገልጿል።