ሙሉዓለም መስፍን የቀድሞው ክለቡን ተቀላቀለ

የአማካይ መስመር ተጫዋቹ ወደ ቀደሞ ቡድኑ አምርቷል፡፡

በተጫዋቾች ዝውውር ላይ በንቃት እየተሳተፈ የሚገኘው የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው ሲዳማ ቡና ከደቂቃዎች በፊት ሙሉዓለም መስፍንን በሁለት ዓመት ውል አስፈርሟል። አምስተኛ ፈራሚ በመሆን ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹ አርባምንጭ ከተማን ከለቀቀ በኃላ ከዚህ ቀደም ወደ ሲዳማ ቡና በማምራት ለሁለት ዓመታት የቻለ ሲሆን በክለቡ በነበረው መልካም ቆይታ መነሻነትም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምርቶ አራት የውድድር ዓመታት አሳልፏል፡፡

ከሁለት ወራት በፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ እገዳ ተጥሎበት የነበረው ሙሉዓለም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ይህን ብሏል:-

“ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተለያየሁበትን ምክንያት በቅርቡ እገልፅላችኋሁ። አሁን ግን ስለ አዲሱ ክለቤ ነው የማወራው፤ ሲዳማ ቡና ቤቴ ነው፡፡ ክለብ መቀየርን ሳስብ የመጀመሪያ ምርጫዬ ያደረኩትም ቤቴ ብዬ የማስበው ቡድን ስለሆነ ነው፡፡ በዚህም ደስታ ተሰምቶኛል። ሌላው ደስ ያለኝ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ የማንሳት ልምድ ካለው አሰልጣኝ ጋር ለመሥራት በመምጣቴ ነው።”