ሀዋሳ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ሾመ

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረትን ለሀድያ ሆሳዕና አሳልፎ የሰጠው ሀዋሳ ከተማ ዛሬ ረፋድ የክለቡ ቦርድ ባደረገው ስብሰባ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል፡፡

የ2013 ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ያጠናቀቀው ሀዋሳ ከተማ የአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረትን ኮንትራት ለማደስ ሁለቱም አካላት ንግግር ቢያደርጉም በጥቅማጥቅም መግባባት ባለመቻላቸው ከቀናት በፊት መለያየታቸው እና አሰልጣኙም ወደ ሀድያ ሆሳዕና ማምራታቸው ይታወሳል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የክለቡ ቦርድ ዛሬ ረፋድ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት የሚመራውን አሰልጣኝ በይፋ መሾሙን ለሶከር ኢትዮጵያ በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

በሁለት ዓመት ውል ክለቡን የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ሆነዋል፡፡ በሲዳማ ቡና የታዳጊ ቡድን ስልጠናን ከጀመሩ በኋላ ከ2010 አጋማሽ እስከያዝነው ዓመት አጋማሽ ድረስ የዋናው ቡድን አሰልጣኝ በመሆን የሰሩ ሲሆን በመጋቢት ወር ላይ ከሲዳማ ከተለያዩ በኃላ አዳማ ከተማን ከሰሞኑ እስከተካሄደው የማሟያ ጨዋታ ድረስ በመምራት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከመለሱ በኃላ በዛሬው ዕለት ደግሞ በይፋ ለሁለት ዓመት የሀዋሳ ከተማ ዋና አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል፡፡