የአስቻለው ታመነ ዝውውር ተጠናቋል

ወደ ፋሲል ከነማ ለማምራት ተቃርቦ የነበረው አስቻለው ታመነ ከደቂቃዎች በፊት ፊርማውን አኑሯል። 

የቀድሞው የዲላ ከተማ እና ደደቢት ተከላካይ ከ2007 ጀምሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ በወጥነት ብቃቱን ሲያሳይ የቆየ ሲሆን በተከታታይ ሁለት ጊዜም የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋችነት ክብርን ማግኘት ችሎ ነበር። አስቻለው ከሁለት ወራት በፊት በቅዱስ ጊዮርጊስ እገዳ ተላልፎበት የቆየ ሲሆን ለረጅም ጊዜ ከፋሲል ከነማ ዝውውር ጋር ስሙ ሲያያዝ ቆይቶ ዛሬ ፊርማውን አኑሯል።

የኢትዮጵያ ብሔሬዊ ቡድን ተከላካይ የሆነው አስቻለው የሁለት ዓመት ውል የፈረመ ሲሆን በፋሲል ከብሔራዊ ቡድን አጣማሪው ያሬድ ባዬ ጋር ጠንካራ ጥምረት እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

ከዝውውሩ መጠናቀቅ በኋላ አስቻለው ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን ብሏል:-

“ወደ አዲሱ ክለቤ ፋሲል ከነማ ስሄድ ብዙ ነገሮችን አጢኜ፣ ከብዙ ሰዎች ጋር ተማክሬ ነው የወስንኩት። ፋሲል ያሉት ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድን አብሬ የምጫወታቸው እና የምግባባቸው ስለሆኑ ስሜን የሚመጥን ክለብ ነው መሄድ ያለብኝ ብዬ ነበር። ፋሲልም ትልቅ ክለብ ከመሆኑ በተጨማሪ በቻምፒየንስ ሊግ የሚወዳደር እና የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ ነው።

“ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መለያየት አልፈልግም ነበር። ብዙ ዓመት ደስ ብሎኝ ተጫውቻለሁ። እውነት ለመናገር የታወቅኩበት፣ ዝናን ያገኘሁበት፣ ኮከብ ተጫዋች የሆንኩበት፣ ራሴን ያሳየሁበት፣ ሀብት ያፈራሁበት፣ ብዙ ነገር ያገኘሁበት ክለቤ ነው ቅዱስ ጊዮርጊስ። ግን እግር ኳስ ነውና አንዳንዴ የሚፈጠረው አይታወቅም። በእንዲህ አይነት ሁኔታ ባልለያይ ጥሩ ነበር። ግን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ኃላፊዎች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በዚህ መልኩ ተለያይቻለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን ከትልቅ ክለብ ወደ ትልቅ ክለብ ነው የተዘዋወርኩት።

“እኔ ፋሲል ከዚህ በተሻለ ውጤታማ ክለብ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ከነበረው ጥንካሬ ላይ እየጨመራቸው ያሉ ልጆችም ጥሩ ናቸው፡፡ እኔም፣ ኦኪኪም፣ ከሪምም መጥተናል። በዚህም የተነሳ በቻምፒየንስ ሊጉ ውጥታማ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ። የምንዘጋጀው የሀገር ውስጥ ዋንጫ ብቻ አይደለም። የሀገር ውስጥ ዋንጫን ደግሞ ከስብስቡ አንፃር የማሳካት አቅም አለው። በክለቡ በሚኖረኝ ቆይታ የታሪክ ተጋሪ ለመሆን ነው እየተዘጋጀው ያለሁት። ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ውጤታማ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ።”

ያጋሩ