ሀዲያ ሆሳዕና የእግድ ውሳኔ ተላለፈበት

ሀዲያ ሆሳዕና በተጫዋቾቹ የቀረበበትን ክስ ተከትሎ የተላለፈበት የእግድ ውሳኔን ተግባራዊ ባለማድረጉ የእግድ ውሳኔ እንደተላለፈበት ታውቋል።

ለረጅም ጊዜያት በዘለቀው የክለቡ እና ተጫዋቾቹ ውዝግብ መነሻነት የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ የቀረበለትን ክስ መርምሮ የዛሬ ወር ክለቡ በአስራ አምስት ተጫዋቾች ላይ የወሰነውን የሁለት ዓመት ዕግድ በመሻር በውላቸው መሠረት ክፍያቸውን እንዲፈፅም መወሰኑ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም ክለቡ ቅሬታውን ለፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ማስገባቱ ይታወሳል።

ይግባኝ ሰሚው የዲሲፕሊን ኮሚቴውን ውሳኔ በማፅናት መልስ በመስጠቱ በሰባት ቀናት ውስጥ ተፈፃሚ እንዲያደርግ ቢወሰንም ክለቡ ተግባራዊ ባለማድረጉ ፌዴሬሽኑ ከሚሰጣቸው ማናቸውም አገልግሎቶች እንዲታገድ መደረጉ ታውቋል።