በዝውውር ገበያው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ቡናማዎቹ የአንድ ዓመት ኮንትራት ካለው ተከላካያቸው ጋር በስምምነት ተለያይተዋል።
በአሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ተጠናክሮ ለመቅረብ ከሰባት ቀናት በፊት በተከፈተው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። ቡድኑ አዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል እንቅስቃሴ ላይ ያለ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ከመሐል ተከላካዩን ምንተስኖት ከበደ ጋር በስምምነት መለያየቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የቀድሞ የአዳማ ከተማ፣ መከላከያ እና መቐለ 70 እንደርታ ተከላካይ የነበረው ምንተስኖት በዘንድሮ የውድድር ዓመት ጅማሮ ቡናማዎቹን ለሁለት ዓመታት ለማገልገል ፊርማውን አኑሮ ነበር። ይህ ቢሆንም ግን በዘንድሮ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 707 ደቂቃዎችን የተጫወተው ተጫዋቹ የአንድ ዓመት ኮንትራት ቢቀረውም በስምምነት ኢትዮጵያ ቡናን ተለያይቷል። ምናልባት ተጫዋቹ የመዲናውን በቡና ስም የሚጠራ ክለብ ለቆ የቀድሞ አሠልጣኙን ለመቀላቀል ወደ ሌላኛው በቡና ስም የሚጠራ ክለብ (ሲዳማ ቡና) ሊያመራ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።