ዋልያ ቢራ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስፖንሰር ሺፕ ስምምነታቸውን አድሰዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስፖንሰር የሆነው ዋልያ ቢራ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት ለመሥራት ከፌዴሬሽኑ ጋር ስምምነት ፈፅሟል።

ራሱን በፋይናንስ ለማጠናከር የተለያዩ ስራዎችን እየከወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዛሬው ዕለት ከሀይኒከን ኢትዮጵያ ጋር በዋልያ ቢራ ምርት በቀጣዮቹ አራት ዓመታት አብሮ ለመስራት ስምምነት ፈፅሟል። ከ11 ሰዓት ጀምሮ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነው ሥነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የሀይኒከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ሁበርት ኢዜ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እና የዋልያ ቢራ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። በቅድሚያም ሁለቱን ተቋማት ወክለው ሚስተር ሁበርት ኢዜ እና አቶ ኢሳይያስ ጂራ የአራት ዓመት ስምምነቱን በይፋዊ ፊርማቸው ፈፅመዋል።

የፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ከተከናወነ በኋላ የስምምነቱን ይዘት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ማብራራት ጀምረዋል። ፕሬዝዳንቱ በገለፃቸውም ዋልያ ቢራ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ወንዶች) በዓመት 15.5 ሚሊዮን ብር በአራት ዓመት ደግሞ 62 ሚሊዮን ብር እንደሚከፍል አስረድተዋል። ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም ይህ ስምምነት ከበፊቱ ውል በ6 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ መሆኑን አውስተዋል።

በመግለጫው ላይ መንግስት የአልኮል መጠጦች እንዳይተዋወቁ ባወጣው መመሪያ ዋልያ ቢራ ተጎጂ እንዳይሆን ከአልኮል ነፃ ምርቶቹን በተለያዩ ትጥቆች ላይ እንዲሰፍር እንደሚደረግ ተገልጿል። ጋዜጣዊ መግለጫን ጨምሮ በፌዴሬሽኑ በኩል የሚዘጋጁ የተለያዩ ዝግጅቶች ላይም ምርቶቹ እንደሚታዩ ተጠቁሟል። ከአቶ ኢሳይያስ ጂራ ንግግር በኋላ የሀይኒከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ሁበርት ኢዜ ተቋማቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስፖንሰር በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ተናግረዋል። ማናጀሩ አክለውም ዋልያ የኢትዮጵያን እግርኳስ ለማሳደግ በድጋሜ ዕድሉን ማግኘታቸውን አንስተው ከፌዴሬሽኑ ጋር የፈፀሙት ስምምነት ጠንካራ እንደሆነ አስረድተዋል።

በመቀጠል ንግግር ለማድረግ ዳግም ዕድሉን ያገኙት አቶ ኢሳይያስ “አንድ ዋና ስፖንሰር መጨመር እንደምንችል ስምምነቱ ላይ አለ። ከዚህ ውጪ እነሱም በፈለግነው ቁጥር ስፖንሰር ቢመጣ ተቃውሞ እንደማያመጡ ተስማምተናል።” የሚል ሀሳብ አንስተዋል። ከቡድኑ ቅፅል ስም እና ከስፖንሰሩ ስም ጋር የተገናኘ ጥያቄ በተከታይነት የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

“ካልተሳሳትኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያ ቅፅል ስሙ ስለሆነ አይደለም ስፖንሰር ያደረጉን። ስፖንሰር ማድረግ ስላለባቸው እንጂ። ብሔራዊ ቡድኑ በሌላ ስምም ቢጠራ የሚያደርጉት ይመስለኛል። ፌዴሬሽናችን ጋር የስም መብት ክፍተት ነበር። ቀድሞ የስም መደራረብ እንዳይመጣ ስራ መሰራት ነበረበት። በየሆነ አጋጣሚ የስም መመሳሰል መጥቷል። ይህ ደግሞ በአጋጣሚ የመጣ ነው እንጂ ታስቦበት አይደለም።”

በመጨረሻ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ለዋልያ ቢራ መልካም አጋጣሚ መሆኑ የተነሳ ሲሆን ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍም ተቋሙ 1.5 ሚሊዮን ብር ለማበረታቻ በፍቃደኝነት ሰጥቶ እንደነበር ተብራርቷል። የተሰጠው ገንዘብም ፌዴሬሽኑ ለቡድኑ አባላት ከሰጠው 6 ሚሊዮን ጋር ተካቶ የተሸለመ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ያጋሩ