ሲዳማ ቡና ስድስተኛ ተጫዋች አስፈርሟል

በዝውውሩ ላይ በፍጥነት እየሠሩ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች የአጥቂ አማካይ አስፈርመዋል፡፡

የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ውል ለማራዘም የተቃረበውና ወደ ተጫዋቾች ዝውውር ጎራ ያለው ሲዳማ ቡና ተክለማርያም ሻንቆ፣ ብሩክ ሙሉጌታ፣ አንዋር ዱላ፣ ተስፋዬ በቀለ እና ሙሉዓለም መስፍንን በያዝነው ሳምንት ወደ ቡድኑ የቀላቀለ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ፍሬው ሰለሞንን በሁለት ዓመት ውል ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል፡፡

የቀድሞው ሀላባ ከተማ፣ ሙገር ሲሚንቶ፣ መከላከያ እና ሀዋሳ ከተማ ታታሪው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ፍሬው የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በወልቂጤ ከተማ ካሳለፈ በኃላ በመከላከያ አሰልጣኙ ከነበሩት ገብረመድኅን ኃይሌ ጋር በጋራ ለመሥራት ዛሬ ለሲዳማ ቡና ፊርማውን አኑሯል፡፡

“በጣም ደስ ብሎኛል። ከቀድሞው አሰልጣኜ ጋር መገናኘቴም ይበልጥ ልዩ ስሜት ፈጥሮብኛል። ዘንድሮ ቡድኑ የማይገባው ቦታ ላይ ሆኖ ጨርሷል። ያንን ለመካስ ክለቡ ጥሩ ዝውውር እያደረገ ነው፡፡ እኔም የተቻለኝን በማድረግ ከጥሩ ውጤት ባለፈ ለዋንጫ ቡድኑ እንዲፎካከር የራሴን ድርሻ እወጣለሁ። በማለት ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳቡን ሰጥቷል፡፡